ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለ ሰላም ንግግር የሰጡትን ገለጻ “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ተቸ

በአማኑኤል ይልቃል

ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራው አማጺ ቡድን፤ የሰላም ንግግርን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትላንት በፓርላማ  ያደረጉት ገለጻ “ሁኔታውን በትክክል ያንጸባረቀ አይደለም” ሲል ተቸ። ከዚህ ቀደም የተደረጉት ሙከራዎች “የሰራዊቱን መኮንኖች እጅ እንዲሰጡ የማግባባት” ስራ እንደሆነ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ መንግስት “ሸኔ” እያለ የሚጠራው አማጺ ቡድን ይህንን ያለው፤ ትላንት ማክሰኞ መጋቢት 19፤ 2015 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። በ“ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ይፋዊ ድረ ገጽ የወጣው እና በቡድኑ አቀባይ ኦዳ ተርቢ በኩል የተሰራጨው ይህ መግለጫ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንትናው ዕለት በተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው የሰጡትን ማብራሪያ አስተባብሏል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሰራዊቱን” የተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት፤ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር እና በክልሉ ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር ይደረጋል የተባለውን የሰላም ንግግር በተመለከተ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። ጥያቄውን ያቀረቡት የፓርላማ አባላት፤ የኦሮሚያ ክልል ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰው፤ ድርድሩ መቼ እንደሚጀምር ጠይቀው ነበር።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሰጠው የሰላም ንግግር ዕድል፤ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል። ከ“ሸኔ” ጋር የሚደረገውን የሰላም ንግግር ለመምራት፤ በፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙንም አስታውቀዋል። መንግስት ባለፉት ሁለት ወራት ገደማ ከታጣቂ ቡድን ጋር ለመነጋገር “ከአስር በላይ ሙከራዎች” ማድረጉንም ገልጸዋል። 

የፌደራል መንግስት እነዚህን ሙከራዎች ቢያደርግም፤ ታጣቂ ቡድኑ “አንድ የተሰባሰበ ኃይል ባለመሆኑ” መቸገራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። የሰላም ንግግሩን አስቸጋሪ ያደረገውም፤ መንግስት የሚያነጋግራቸው የቡድኑ ኃይሎች “የተለያዩ ሀሳብ እና አቋም ይዘው ስለሚመጡ” እንደሆነም አብራርተዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ግን በታጣቂ ቡድኑ ተቀባይነት አላገኘም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፓርላማ ማብራሪያ ተከትሎ መግለጫ ያወጣው አማጺው ቡድን፤ የ“ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” አመራርን ለማነጋገር ተደረጉ የተባሉት ጥረቶች “በቅንነት የተካሄዱ አልነበሩም” ብሏል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት “በርካታ የአገር ውስጥ አሸማጋይ ኮሚቴዎችን ማሰማራቱን” ያረጋገጠው መግለጫው፤ ሆኖም ሂደቱ የሰራዊቱን መኮንኖች በግለሰብ ደረጃ “እጅ እንዲሰጡ ለማሳመን” የተደረገ እንደነበር ገልጿል። ሙከራውም “አልተሳካም” ብሏል። 

ይህ አይነቱ አካሄድ፤ መንግስት ከዚህ ቀደም ታዋቂ ግለሰቦች በመጠቀም “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ለመበተን ካደረገው ያልተሳካ ሙከራ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው” ሲልም አማጺ ቡድኑ ወንጅሏል። “እንዲህ አይነት ድርጊቶች እንደ እውነተኛ የሰላም ድርድር ሙከራ ሊታዩ አይችሉም” ያለው የሰራዊቱ መግለጫ፤ “ይልቁንም የሰላም ተስፋውን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረግ ዘመቻን የሚወክሉ ናቸው” ሲል በሂደቱ ላይ ያለውን ተቃውሞ አንጸባርቋል። 

“የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” በዚሁ መግለጫው፤ ታጣቂ ቡድኑ “አንድ የተሰባሰበ ኃይል” አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ ላቀረቡት ገለጻ ምላሽ ሰጥቷል። “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በከፍተኛ እዝ” እንደሚመራ እና ይህንንም “መንግስት በሚገባ የሚያውቀው” መሆኑን አማጺ ቡድኑ በመግለጫው ጠቅሷል። ሰራዊቱ “ለድርድር በማያመች መልኩ እጅጉን ያልተማከለ” እንደሆነ በማስመሰል፤ መንግስት “አዲስ የፕሮፖጋንዳ ትርክት” የመፍጠር ሙከራ እንዳያደርግም አሳስቧል።

አማጺ ቡድኑ “አሁንም ለንግግር ቁርጠኛ መሆኑን” በመግለጫው ቢያስታውቅም፤ ከዚህ ቀደም በቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጠውን ጉዳይ በድጋሚ አስተጋብቷል። የኦሮሚያ ክልል ለ“ሸኔ” የሰላም ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ “ሰራዊቱ” ባወጣው መግለጫ፤ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጦ ነበር። የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ፤ የሰላም ንግግሩ “በፌደራል መንግስት መመራት አለበት” የሚል ነው።

ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ፤ ከፌደራል መንግስት ጋር የሚደረገው ይህ የሰላም ንግግር “ሶስተኛ ወገን” የሆኑ ዓለም አቀፍ አካላት እንዲሳተፉበት የሚጠይቅ ነው። አማጺ ቡድኑ ዓለም አቀፍ አካላት እንዲሳተፉ የፈለገው “ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ዋስትና መስጠት” የሚችሉ አካላት ናቸው የሚል መከራከሪያን በማቅረብ ነው። በትላንቱ “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” መግለጫ ላይም ይኸው ቅደመ ሁኔታ በድጋሚ ቀርቧል። 

“ወደፊት ሊካሄድ የሚችል የሰላም ስምምነትን ስኬታማነትን ለማረጋገጥ፤ የአለም አቀፍ የሶስተኛ ወገን ሽምግልና አስፈላጊነት” ላይ “የሰራዊቱ” አቋም አለመቀየሩን በመግለጫው ላይ ተመላክቷል። “ተገቢው ገለልተኛ አለም አቀፍ የሶስተኛ ወገንን” ያሳተፈ የሰላም ንግግር ለማካሄድ “አዎንታዊ ምልክቶች” እንዳሉም አማጺ ቡድኑ በመግለጫው አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር በሚደረግ የሰላም ንግግር፤ ዓለም አቀፍ አካላት እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ሀሳብ የተነሳው “በሰራዊቱ” ብቻ አይደለም። ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የፓርላማ አባላት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለአፍሪካ ህብረት በጻፉት ደብዳቤም ይህንኑ ጠይቀዋል። የፓርላማ አባላቱ በዚሁ ደብዳቤያቸው፤ የአፍሪካ ህብረት በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን “ታጣቂ ኃይል” እና መንግስትን እንዲያደራድር መጠየቃቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)