የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሰባት ሀገራት 331 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ወሰነ

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ “በርካታ እና ተደራራቢ ሰብዓዊ ቀውሶች” ለተጋረጠባቸው ሰባት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት 331 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ወሰነ። በእነዚህ ሀገራት ያሉ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ህብረቱ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 20፤ 2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከሰባቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ከፍተኛውን ገንዘብ የመደበው ለደቡብ ሱዳን ነው። በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ከ9.4 ሚሊዮን የደቡብ ሱዳን ህዝብ 76 በመቶው አስቸኳይ እርዳታ ፈላጊ ነው። በተለያዩ የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች ከበረታው ግጭት በተጨማሪ፤ ከከባቢ አየር ለውጥ ጋር የተያያዙ ቀውሶች የሀገሪቱን ሰብዓዊ ቀውስ አባብሰዋል። ይህንን ታሳቢ ያደረገው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን፤ ለደቡብ ሱዳን 82 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት መወሰኑን ገልጿል። 

የህብረቱ ኮሚሽን ተመሳሳይ የፖለቲካ ቀውስ ለበረታባት ሱዳን 73 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል። እንደ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ሁሉ ኢትዮጵያን ለምትጎራበተው ሶማሊያ፤ በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የተመደበው የገንዘብ መጠን 72 ሚሊዮን ዩሮ ነው። ኢትዮጵያ ከህብረቱ ኮሚሽን እንድታገኝ የተወሰነላት የሰብዓዊ እርዳታ 60.5 ሚሊዮን ዩሮ ነው። የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት፣ ድርቅ፣ ከፍተኛ የህዝብ መፈናቀል እና የስደተኞች ፍልሰት እንዲሁም ተጨማሪ አካባቢያዊ ግጭቶች፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት መፍጠሩን አብራርቷል። 

የአውሮፓ ኮሚሽን ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ከመደበው ገንዘብ 8 ሚሊዮን ዩሮው የሚውለው ለአደጋ ዝግጁነት መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል። የሰላማዊ ሰዎች ደህንነት ጥበቃ፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚከናወኑ ስራዎች፣ የምግብ ዋስትና፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና በአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ትምህርት፤ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በቀጠናው ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው። የስደተኞች እና የተፈናቀሉ ሰዎች አስቸኳይ ፍላጎቶች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው የህብረቱ ኮሚሽኑ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ መከበር እና ማሳደግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)