የመከላከያ ሰራዊት፤ ለሁለት ዓመት ገደማ በታጣቂዎች ስር የቆየውን የአበርገሌ ወረዳ ዋና ከተማ ዳግም ተቆጣጠረ 

በአማኑኤል ይልቃል

ላለፉት 21 ወራት በህወሓት እና በአገው ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ ታጣቂዎች ይዞታ ስር የቆየችውን የአበርገሌ ወረዳ ዋና ከተማን፤ የመከላከያ ሰራዊት መልሶ ተቆጣጠረ። የመከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር ወደምትገኘው “ንየር አቑ” ከተማ የገባው፤ ታጣቂዎቹ አካባቢውን በትላንትናው ዕለት ለቅቀው ከወጡ በኋላ እንደሆነ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የትግራይ ክልል አጎራባች የሆነው የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አበርገሌ እና ጻግብጂ የተባሉት ወረዳዎቹ ከቁጥጥሩ ውጭ ሆነው ቆይተዋል። ጦርነቱ በተጀመረ “በአጭር ጊዜ” ውስጥ በህወሓት ታጣቂዎች እጅ ገብተው የነበሩት ሁለቱ ወረዳዎች፤  ለመጀመሪያ ጊዜ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር የገቡት የፌደራል ጦር የትግራይ ክልልን ሲቆጣጠር ነበር።  

ይሁንና የፌደራሉ መንግስት በሰኔ 2013 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ሲወጣ፤ ሁለቱ ወረዳዎች ዳግም በህወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ለመውደቅ ተገድደዋል። ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር በአማራ ክልል እና አፋር ክልሎች ሲዋጋ የቆየው የመከላከያ ሰራዊት በአማጽያኑ እጅ የነበሩ በርካታ ቦታዎችን ቢያስለቅቅም፤ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር ያሉት ሁለት ወረዳዎች ግን በታጣቂዎች ተይዘው ቆይተዋል።

የፌደራል መንግስት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከህወሓት ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመ በኋላም ጭምር፤ ሁለቱ ወረዳዎች በታጣቂዎች ይዞታ ስር መቆየታቸው በአማራ ክልል ጥያቄ ማስነሳቱ ይታወሳል። ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ በተደረገው የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ይኸው ጉዳይ ተነስቶ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ሁለቱን ወረዳዎች የተመለከቱ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፤ አካባቢዎቹ ነጻ ያልወጡበትን ምክንያት አስረድተዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ “ከህወሓት ጋር በመሆን ሲንቀሳቀስ” ነበር ያሉት “የአገው ሸንጎ ቡድን”፤ ሁለቱን ወረዳዎች ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ለክልሉ ምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። የአማራ ክልል መንግስት በጻግብጂ እና አበርገሌ ወረዳዎች ያለውን ችግር ለመፍታት፤ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች ጋር የሰላም ንግግር ማካሄድ መጀመሩንም በወቅቱ አስታውቀው ነበር። ከታጣቂዎቹ ጋር የተጀመረው የሰላም ንግግር ለሁለት ጊዜያት ያህል መካሄዱን የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ከሶስት ሳምንት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መናገራቸው ይታወሳል።

የክልሉ መንግስት በአካባቢው ሰላም ለማስፈን፤ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከፌደራል መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራ የቢሮ ኃላፊው በወቅቱ መግለጻቸውም አይዘነጋም። “ከአገው ሸንጎ” ታጣቂዎች ጋር ተጀምሮ የነበረው የሰላም ንግግር “አለመሳካቱን” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ስቡህ ገበያው፤ ሆኖም በመከላከያ ሰራዊት እና የህወሓት ጀነራሎች መካከል የተደረገ ውይይት ውጤት ማምጣቱን አስረድተዋል። 

በሁለቱ አካላት መካከል በትላትናው ዕለት የተካሄደው ውይይት ትኩረት ያደረገው “በሰላም ጉዳይ” እና “ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ ስለሚቻልባቸው” መንገዶች እንደነበር የአበርገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ክፍሌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህንን ውይይት ተከትሎም፤ ራሱን “የአገው ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ” በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት የዚያኑ ዕለት ንየር አቑ ከተማን ለቅቀው መውጣታቸውን አክለዋል።  

“የወረዳው ዋና ከተማ ሙሉ ለሙሉ ነጻ ሆኗል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት ትላንት ገብቶ አድሯል። እኛ ዛሬ እዚያው ነው ያለነው። ያለ ምንም ተኩስ፤ የመከላከያ ሰራዊት በሰላም ከተማውን ተቆጣጥሮታል” ሲሉ አቶ አለሙ በዛሬው ዕለት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል። የመከላከያ ሰራዊት ንየር አቑ ከተማ መግባቱን ተከትሎ፤ “የተወሰኑ” የታጣቂ ቡድኑ አባላት “ተሳስተን ነበር” በማለት እጃቸውን መስጠታቸውን ጨምረው ገልጸዋል። 

በከተማዋ ውስጥ የህወሓት ታጣቂዎች የነበሩ ስለመሆኑ ጥያቄ የቀረበላቸው የአበርገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ፤ “እኛ ትንሽ ዘግይተን፣ አርፍደን ነው የገባነው። የመከላከያ ኃይሉ ነው ይህንን ሊያውቅ የሚችለው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በአበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች “በፊት አመራር የነበሩ የታጣቂ የህወሓት ኃይሎች እንዳሉ” በመረጃዎች መረጋገጡን የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀው ነበር። 

አሁን በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር የምትገኘው ንየር አቑን፤ ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና ከተማ ሰቆጣ 67 ኪሎሜትር ላይ የምትገኝ ናት። ከሰቆጣ ወደ ንየር አቑ ከተማ ለመድረስ ሁለት ቀበሌዎችን ማቋረጥ እንደሚገባ የገለጹት አቶ አለሙ፤ እነዚህ ሁለት ቀበሌዎች ከታጣቂዎች ነጻ መሆናቸውን አስረድተዋል። በቀጣይም ሌሎች የአበርገሌ ቀበሌዎች “ነጻ ይሆናሉ” የሚል ተስፋ እንዳለም ገልጸዋል። አበርገሌ ወረዳ በአጠቃላይ 17 ቀበሌዎች አሉት። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)