የፌደራል መንግስት፤ ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማ ለመልቀቅ መስማማቱን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ

በአማኑኤል ይልቃል

የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል በጀት ለማስተላለፍ ከስምምነት ላይ መድረሱን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ለትግራይ ክልል የሚለቀቀውን የገንዘብ መጠን በተመለከተ ግን “ገና ውይይት እንደሚካሄድ” ገልጸዋል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመስከረም 2013 ባስተላለፈው ውሳኔ የተቋረጠው ለትግራይ ክልል የሚሰጥ የበጀት ድጎማ እንዲለቀቅ ከስምምነት ላይ የተደረሰው፤ ክልሉን የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙን ተከትሎ ነው። ለትግራይ ክልል የሚሰጠው የበጀት ድጋፍ እንዲቋረጥ የተደረገው፤ ክልሉ ከፌደራል መንግስት እውቅና ውጭ “ኢ-ህገ መንግስታዊ ምርጫ አካሄዷል” በሚል ነው። 

በጳጉሜ 2012 በትግራይ ክልል በተካሄደ ምርጫ አማካኝነት የተቋቋመውን የክልሉን መንግስት “ህገ ወጥ” ያለው የፌደራል መንግስት፤ ግንኙነቱን አቋርጦ ቆይቷል። በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ይበልጡኑ የሻከረው የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ክልል መንግስት ግንኙነት እንደገና የመታደስ አዝማሚያ ያሳየው፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ግጭትን የማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው።

በስምምነቱ መሰረት እንዲቋቋም የተደረገውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሩ አቶ ጌታቸው ረዳ መሾማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያስታወቁት ባለፈው ሳምንት መጋቢት 14፤ 2015 ነበር። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር “የክልሉን ስራ አስፈጻሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር” ኃላፊነት እንደተጣለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አቶ ጌታቸው የሚያዋቅሩት ጊዜያዊ አስተዳደር “በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ፖለቲካ ኃይሎችን ውክልና ያረጋገጠ እና አካታች” እንደሚሆን ተገልጿል። ከተሾሙ በነገው ዕለት አንድ ሳምንት የሚሞላቸው አቶ ጌታቸው፤ 11 የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላትን ይዘው ከፌደራል መንግስት ጋር ለመነጋገር በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ የህወሓት አባላትን፣ ወታደራዊ አመራሮች እና ምሁራንን ያካተተ ነው። 

በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት አቶ ጌታቸው፤ ለክልሉ የሚለቀቅ በጀትን አስመልክቶ ከፌደራሉ መንግስት ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። የፌደራሉ መንግስት ለክልሉ ሊለቅ ያሰበውን የበጀት መጠን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ቢያስታውቅም፤ ጉዳዩ የተቋጨ አለመሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። “በጀት ተፈቅዷል። [ትክክለኛ] ቁጥሩን በሚመለከት ግን ገና እንነጋገራለን” ሲሉ የሁለቱ አካላት ንግግር ያለበትን ደረጃ ጠቁመዋል።

የፌደራል መንግስት የ2015 ዓመትን በጀት ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ሲያጸድቅ፤ ለትግራይ ክልል 13.3 ቢሊዮን ብር መመደቡ ይፋ ተደርጎ ነበር። ከዚህ በጀት ውስጥ 12.42 ቢሊዮን ብሩ ለክልሉ የሚሰጥ የፌደራል መንግስት ድጎማ ሲሆን፤ ቀሪው ገንዘብ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረበውን የ2015 በጀት አስመልክቶ ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ባካሄዱት ውይይት ወቅት ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ፤ በጀቱ ለትግራይ ክልል የሚተላለፍበት መንገድን የተመለከተ ነበር። በጊዜው በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ የትግራይ ክልል “በሕገ መንግስት እውቅና ያለው” በመሆኑ በክልሎች የበጀት ድልድል መካተቱን ተናግረው ነበር። ሆኖም በጀቱ የሚተላለፈው “ህገ መንግስታዊ እና ህጋዊ ስርዓት” ሲሟላ እንደሆነ ለፓርላማ አባላቱ በወቅቱ መናገራቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ለዚህ ዘገባ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ተስፋለም ወልደየስ አስተዋጽኦ አድርጓል]