በሃሚድ አወል
በኢትዮጵያ ዝቅተኛ ወርሃዊ የደመወዝ ወለልን ለመደንገግ የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ጸድቆ ወደ ስራ አለመግባቱ በተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥያቄ አስነሳ። የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ በውጭ ሀገር ለሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን የሚከፈለው “አነስተኛ” ወርሃዊ ደመወዝ እንዲስተካከል ለማድረግ የታሰበ ነገር ስለመኖሩም ጠይቀዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሁለቱን ጥያቄዎች ያነሳው፤ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የ8 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ ነው። ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን ትላንት ረቡዕ መጋቢት 20፤ 2015 ያቀረቡት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ መስሪያ ቤታቸው ከውጭ ሀገር ስራ ስምሪት፣ ከቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና እንዲሁም ከስራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
ከሚኒስትሯ ማብራሪያ በኋላ የቋሚ ኮሚቴው ያዘጋጃቸው ጥያቄዎች በጽሁፍ ቀርበዋል። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል “ዝቅተኛ የደመወዝ መነሻ እርከን ለመደንገግ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱ የተገለጸ ቢሆንም በትኩረት ተይዞ ጸድቆ ስራ ላይ እንዲውል የማይደረገው ለምንድን ነው?” የሚለው ይገኝበታል። አቶ ፍሬው ተስፋዬ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፤ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ የቆየ አጀንዳ መሆኑን አንስተው “እስከ መቼ ነው ይሄ ጉዳይ እየተንከባለለ የሚሄደው?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ እርከንን ለመደንገግ ደንብ መዘጋጀቱ የተገለጸው፤ ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት በመስከረም 2013 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ መስሪያ ቤትን ይመሩ የነበሩት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ “ዝቅተኛ ደመወዝ የሚወስን የደመወዝ ቦርድ ስለሚቋቋምበት ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ አልቋል” ብለው ነበር። ይህንን ደንብ በተመለከተ ትላንት በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት፤ በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ አሰግድ ጌታቸው ናቸው።
ሚኒስትር ዴኤታው፤ ደንቡ ሳይጸድቅ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስያሜውን ቀይሮ እንደገና መደራጀቱን ገልጸዋል። የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ከተዋቀረ በኋላ፤ በረቂቅ ደረጃ ያለው ደንብ አሁን እርሳቸው ወዳሉበት መስሪያ ቤቱ ተመልሶ ማሻሻያዎች እንደተደረጉበት አመልከተዋል። ሚኒስትር ዲኤታው አክለውም፤ “ሰነዱን revise አድርገን ወደ በላይ አመራር ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው ያለነው” ሲሉ ረቂቅ ደንቡ ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ “የሀገር ውስጥ ቀጣሪዎች የመክፈል አቅም እና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ምን ይመስላል?” የሚሉትን እሳቤዎች ያካተተ ጥናት እያደረገ መሆኑንም አቶ አሰግድ ጠቁመዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት በበኩላቸው “እንዴት እንፈጽመው ምን ያጋጥመናል የሚለውን ለመለየት የምናጠናው እንጂ፤ ይሁን አይሁን የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አይደለም” ሲሉ የጥናቱን ፋይዳ አብራርተዋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ማብራሪያቸው ምላሻቸው፤ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን ከህግ ማዕቀፍ በተጨማሪ የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ሊቀየር እንደሚገባ ጠቁመዋል። “ድህረ ጦርነት ኢኮኖሚ ነው እየመራን ያለነው” ያሉት ሙፈሪያት፤ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን በተመለከተ “ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት የሚቻልበት ሀገራዊ ሁኔታ አይደለም ያለው” ብለዋል።
ከአራት አመት በፊት የወጣው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ፤ ዝቅተኛ ደመወዝን የሚወስን የመንግስት የአሰሪና ሰራተኛ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት “የደመወዝ ቦርድ” እንደሚቋቋም ይደነግጋል። ቦርዱን የሚያቋቁመው እንዲሁም ተግባር እና ኃላፊነቱን የሚወስነው ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚወጣም አዋጁ ያታትል። ይህን አዋጅ በመንተራስም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ዓመት የዓለም ሰራተኞችን ቀንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ “መንግስት በአዋጁ የተጠቀሱትን እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ “በአስቸኳይ ጥረት እንዲያደረግ” ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ዘላቂነት ያለው ኑሮን ለማረጋገጥ እና ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን በኢትዮጵያ ለመሳብ፤ ዝቅተኛ የደመወዝ ፖሊሲ ማውጣት ቁልፍ መሆኑን የአለም አቀፉ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ከሁለት ወራት በፊት ባዘጋጀው ውይይት ላይ ተገልጾ ነበር። የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በሰራው የ2013 የሰራተኛ ኃይል እና የፍልሰተኞች ዳሰሳ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሰራተኞች የሚከፈለው ያልተጣራ አማካይ ወርሃዊ ደመወዝ 4,127 ብር ነው።
በተመሳሳይ በአለም አቀፉ ሰራተኞች ድርጅት ዳሰሳ መሰረት፤ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወደ 40.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰራተኞች ነበሩ። በዳሰሳው መሰረት በከተማ ውስጥ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሰራተኞች 46 በመቶ ሲሆኑ፤ በገጠር ውስጥ ደግሞ 5 በመቶ ብቻ ናቸው። ከአጠቃላይ የደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች ውስጥ 48 በመቶ የሚሆኑት በመንግስት ዘርፍ፤ ቀሪዎቹ 52 በመቶ ደግሞ በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው ይሰራሉ።
በትላንቱ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ፤ ከዝቅተኛ ደመወዝ ወለል በተጨማሪ በውጭ ሀገር ለሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን የሚከፈለው “አነስተኛ ወርሃዊ ደመወዝን” የተመለከተ ጥያቄም ቀርቧል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ በውጭ ሀገር ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ሀገር ዜጎች “ያነሰ ክፍያ” እንደሚያገኙ ጠቅሰዋል። ይህን በተመለከተ የስራ፣ ስራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ንጉሱ ጥላሁን “ልዩነቱ የአቅም ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ላይ “ተወዳዳሪ እና ብቃት ያለው ሰው የሚፈለግ መሆኑን” የጠቀሱት አቶ ንጉሱ፤ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች “ማብቃት” ላይ ጉድለት እንዳለ አስረድተዋል። በውጭ ሀገር ለስራ የሚሰማሩ የፊሊፒንስ ዜጎች “የተማሩ፣ ከዩኒቨርስቲ እና ኮሌጆች የተመረቁ በመሆናቸው” ከቤት ሰራተኝነት በተጨማሪ “የአስተዳደር ስራ ይሰራሉ” ሲሉ ሃሳባቸውን በምሳሌ አስደግፈው አስረድተዋል። ኢትዮጵያውያን ዜጎች “ተፈላጊ እንዲሆኑ እዚህ ማብቃት አለብን” ሲሉ መስሪያ ቤታቸው በመፍትሔነት የያዘውን ሃሳብ ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያትም በተመሳሳይ፤ “ብቃት ያለው ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ካልላክን ክፍያው ላይ የመደራደር አቅማችን በዚያው ልክ ነው አነስተኛ የሚሆነው” ብለዋል። በዚህም መሰረት ተቋማቸው፤ “የሰለጠነ” እና “ከፊል የሰለጠነ” የሰው ኃይል ወደ ውጭ ለስራ ለማሰማራት በሂደት ላይ መሆኑን አንስተዋል። አቶ ንጉሱ በበኩላቸው፤ ለስራ የሚሰማሩ ዜጎችን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በምታደርገው የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ተገቢው ደመወዝ እና መሰል “መብቶች ስለመረጋገጣቸው ነው የምንንጋገረው” ሲሉ ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)