አዋጅን “በተጻረረ መንገድ” የተሾሙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ከኃላፊነት እንዲነሱ ኢዜማ ጠየቀ

በአማኑኤል ይልቃል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን “በተጻረረ መንገድ” የሾሟቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ከኃላፊነት እንዲያነሱ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጠየቀ። መንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን “ነጻ እና ገለልተኛ” ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራም ፓርቲው አሳስቧል።

ኢዜማ ይህንን ጥያቄ ያቀረበው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መጋቢት 19 በተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት “የሃሳብ የበላይነትን” በተመለከተ ለሰጡት ማብራሪያ በሰጠው ምላሽ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማክሰኞው የፓርላማ ውሏቸው፤ “አሁን ያለውን መንግስት መቀየር የሚቻለው ሻል ያለ የሚጨበጥ ሀሳብ ሲመጣ” መሆኑን ተናግረው ነበር። 

አብይ በሀገሪቱ ውስጥ “ነጻ ሚዲያ፣ ነጻ ሀሳብ እና ነጻ ምርጫ” እንዲኖር ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አንስተው፤ “ስልጣን በኮሮጆ እንጂ በመናጆ አይያዝም” ሲሉ ተደምጠዋል። “ፓርቲዎች መዘጋጀት ያለባቸው ሀሳብ ለማምጣት ነው። አሁን ሀሳብ የለም… ሰብሰብ ብሎ፣ ሀሳብ ይዞ፣ ያን ወደ ህዝብ አቅርቦ፣ ለመመረጥ እና ለማሸነፍ የሚደረግ ጥረት ለሁላችን የሚጠቅመን ይሆናል” ሲሉም ለፖለቲካ ፓርቲዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። 

ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ምላሽ የሰጠው ኢዜማ፤ “የሃሳብ የበላይነትን ለማሳየት የመጫወቻ ሜዳ ከሆኑት መካከል ዋነኛ የሆኑትን የሚዲያ ተቋማትን አፍኖ የገዢው ፓርቲ ልሳን በማድረግ፤ የሚሉትን አይነት የሃሳብ የበላይነት ያለው መንግስት አስቸጋሪ መሆኑን [ይወቁት]” ብሏል። በማህበረሰቡ ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው የህዝብ መገናኛ ብዙሃን፤ “ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ስር በመውደቃቸው ለሃሳቦቻችን እድል ነፍገውናል” ሲል ኢዜማ በምላሹ ጠቅሷል። 

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ለፓርቲ ዕድል በሚሰጡበት ጊዜ እንኳን “እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ መስራት፣ ማህበረሰቡ ለድርጅታችን ያለውን አረዳድ እና በየጊዜው የሚወስዳቸውን አቋሞችና የመፍትሔ ሃሳቦች ተደራሽነት በእጅጉ ጎድተውታል” ሲል ፓርቲው ከስሷል። በዚህም ምክንያት የፓርቲውን ሃሳብ መስማት ከሚፈልጉ ወገኖች እና ከአባላቶቹ ጭምር “በቂ ስራ አልሰራችሁም” የሚል ወቀሳ እንደሚሰነዘርበትም አስታውቋል። 

የሃሳብ የበላይነት ያለው ወገን ተገቢውን ዕድል እንዲያገኝም፤ መንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት “ነጻ እና ገለልተኛ” እንዲሆኑ “ልዩ ትኩረት ሰጥቶ” መስራት እንዳለበትም ኢዜማ አሳስቧል። የፌደራል መንግስት ከመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ፍላጎቱ ካለው፤ ሁለት “እርምቶችን” መውሰድ እንዳለበት ኢዜማ በዛሬው ምላሹ ጠቁሟል። 

ፓርቲው በቀዳሚነት የጠቀሰው፤ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተሹመው በፓርላማ ሹመታቸው የጸደቀላቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላትን ጉዳይ ነው። ዘጠኝ አባላት ያለው ይህ ቦርድ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴንን እና የቱሪዝም ሚኒስትሯን ናሲሴ ጫሊን በአባልነት የያዘ ነው። የቦርዱ አባል ከሆኑት ዘጠኝ ግለሰቦች ውስጥ አራቱ የብልጽግና ፓርቲ አባል ሲሆኑ፤ ይህም ሹመቱ “የመገናኛ ብዙሃን አዋጁን የጣሰ ነው” የሚል ትችት እንዲቀርብበት አድርጓል። 

በ2013 ዓ.ም የወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ የቦርድ አባላት የሚመረጡበትን መስፈርት በዘረዘረበት ክፍል ላይ፤ በእጩነት የሚቀርቡ ግለሰቦች “የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ” መሆን እንደሌለባቸው ደንግጓል። የዛሬ ዓመት ገደማ የተሾሙትን የቦርድ አባላት ጉዳይ በዛሬው መግለጫው ያነሳው ኢዜማ፤ ሹመቱ የተከናወነው አዋጁን “በተጻረረ መንገድ” መሆኑን አስታውሷል። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን በተጻረረ መንገድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት አድርገው የሾሟቸውን የፓርቲያቸውን አመራር አባላት ከተቋማቱ በማንሳት ቁርጠኝነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል” ብሏል ኢዜማ።

ፓርቲው “እርምት እንዲወሰድበት” የጠየቀው ሌላኛው ጉዳይ፤ “ባለቤትነታቸው በውል የማይታወቁ” እና “የፓርቲ ልሳን” ሲል የጠራቸውን የመገናኛ ብዙሃንን የተመለከተ ነው። ኢዜማ መገናኛ ብዙሃኑን በስም ከመጥቀስ ቢቆጠብም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተቋማቱን “ምንነት እና ሕጋዊነት” ለህዝብ ግልጽ እንዲያደርጉ ግን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አላለም። 

ቀደም ሲል በኢህአዴግ አሁን ደግሞ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ “ልሳን በመሆን ያገለግላሉ” በሚል ትችት ከሚቀርብባቸው መገናኛ ብዙሃን መካከል፤ ፋና እና ዋልታ ይጠቀሳሉ። በሁለቱ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬቶች ስር የሚተዳደሩ የቴሌቪዥን እና ራዲዮ ጣቢያዎች በንግድ ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ አግኝተው የተመዘገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)