በሃሚድ አወል እና አማኑኤል ይልቃል
በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ክሳቸው መቋረጡን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ። የፍትህ ሚኒስቴር ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 21፤ 2015 ባወጣው መግለጫ፤ ከግጭቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂነት በተመለከተ “በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ” ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው በህወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶ የነበረው ክስ የተቋረጠው፤ በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት መሆኑን ጠቁሟል። ከአምስት ወራት በፊት ጥቅምት 23፤ 2015 በፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመው ይህ የሰላም ስምምነት፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ተጠያቂነትን ያማከለ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው” አስፍሯል።
የሽግግር እርምጃዎችን የሚያትተው የሰላም ስምምነቱ ክፍል፤ ተግባራዊ የሚደረገው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ “እውነትን ማረጋገጥ እንዲሁም እርቅ እና ለተጎጂዎች መፍትሔ መስጠት ላይ ያተኮረ ሊሆን እንደሚገባው” አቅጣጫ አስቀምጧል። የፍትሕ ሚኒስቴር በዚህ ስምምነት መሰረት የህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ክስ ማቋረጡን ቢገልጽም፤ ክሳቸው የተቋረጠላቸው አመራሮችን ብዛትም ሆነ በየትኛው መዝገብ የተከሰሱ አመራሮች ስለመሆናቸው ያለው ነገር የለም።
ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀስ በኋላ ፍትሕ ሚኒስቴር ከከፈታቸው የክስ መዝገቦች መካከል፤ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚጠራው መዝገብ አንደኛው ነው። በዚህ መዝገብ አራት ድርጅቶች እና 52 ግለሰቦችን ጨምሮ 62 ተከሳሾች ተካትተው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በነበሩ አመራሮች ላይ የተከፈቱ ሌሎች የክስ መዝገቦችም፤ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።
በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ ክስ ከተመሰረተባቸው 52 ግለሰቦች መካከል፤ ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳን ስምንት የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ይገኙበታል። የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ በሐምሌ 2013 ዓ.ም ሁለት ክሶችን ሲመሰርት፤ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት 21 ተከሳሾች ብቻ ነበሩ። ቀሪ 37 ግለሰቦች ላለፉት አንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበረው በሌሉበት ነው።
የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በ62ቱ ተከሳሾች ላይ ያቀረበው ክስ፤ በሕገ መንግስትና በሕገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን እንዲሁም የሽብርተኝነት ድርጊቶች ፈጽመዋል የሚል ነበር። ተከሳሾቹ ላይ ከቀረበባቸው ክስ የመጀመሪያው፤ በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ፣ ኢ-ሕገመንግስታዊ ምርጫ በማካሄድ፣ በሕገ-መንግስት የተቋቋመ እና እውቅና ያለውን የክልል መንግስት የመለወጥ ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው። በተከሳሾቹ ላይ ቀርቦ የነበረው ይህ ክስ ከዕድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት እንደሚስቀጣ በወንጀል ህጉ ላይ ተቀምጧል።

ሁለተኛው ክስ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ የቀረበ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ “የፌዴራል መንግስትን በመሳሪያ ጥቃት የመለወጥ” ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው። ተከሳሾቹ ይህን ዓላማ ለማሳካት፤ “የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ” የተባለ የጦር ኃይል በማደራጀት፣ በፌዴራል መንግስት እና የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውም ክሳቸው ያትታል። ይህ ክስ ከ15 ዓመት እስራት ጀምሮ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት የሚያስቀጣ ነው።
በዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ ክሳቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ መካከል ስድስት ግለሰቦች “የጤና እና የዕድሜ ሁኔታቸውን ከግምት በማስገባት” ክሳቸው እንዲነሳላቸው መደረጉን ፍትሕ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ አስታውቆ ነበር። በዚህ ምክንያት ክሳቸው የተቋረጠላቸው፤ አቶ ስብሐት ነጋ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር እና ወ/ሮ ኪሮስ ሐጎስ ናቸው። ስድስቱ ግለሰቦች ክሳቸው ከተቋረጠ በኋላ ቀሪዎቹ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]