በአማኑኤል ይልቃል
በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና በሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ መዝገብ ተከስሰው በእስር ላይ የነበሩ የህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 21፤ 2015 አመሻሽ ላይ ከእስር መፈታታቸውን የተከሳሾቹ ጠበቆች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሃፍቶም ከሰተ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በዛሬው ዕለት ከእስር ተለቅቀው ወደ ቤታቸው መግባታቸው ከተረጋገጡ ተከሳሾች ውስጥ፤ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እና ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ እንደሚገኙበት ጠበቃው አስታውቀዋል።
ተከሳሾቹ ዛሬ አመሻሽ ላይ በእስር ላይ ከቆዩበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወደ ሲ.ኤም.ሲ የመኖሪያ ግቢ፣ ፒያሳ እና ሳሪስ አካባቢዎች በማረሚያ ቤቱ አውቶብስ ከተወሰዱ በኋላ መፈታታቸውን ጠበቃው አስረድተዋል። እስረኞቹ ወደ እነዚህ ቦታዎች እንደተወሰዱ አስቀድሞ የተነገራቸው ቤተሰቦች፤ በስፍራው ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል ተብሏል።
ዛሬ ከእስር የተፈቱት በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ የተካተቱ 16 ተከሳሾች እና በሌተናል ጄነራል ታደሰ መዝገብ ስር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ 20 ወታደራዊ መኮንኖች መሆናቸውን ጠበቃ ሃፍቶም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። እነዚህ ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ከእስር የተለቀቁት፤ በዐቃቤ ሕግ ቀርቦባቸው የነበረው የወንጀል እና የሽብር ድርጊት ክስ መቋረጡን ፍትሕ ሚኒስቴር ባስታወቀ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።
በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ክስ የተቋረጠው፤ ከሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂነት “በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ” ከስምምነት ላይ በመደረሱ ምክንያት መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ይህን መግለጫ ከማውጣቱ ሰዓታት አስቀድሞ፤ በዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች ከዚህ ቀደም በተሰጠ ቀጠሮ መሰረት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ተከሳሾች ክሳቸውን በተመለከተ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጓሜ በመጠየቃቸው፤ የምክር ቤቱን ምላሽ ለመጠባበቅ በሚል ነበር። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጓሜ ትርጉም እንዲሰጥበት የተጠየቀው የተከሳሾች አቤቱታ፤ “ትግራይ ውስጥ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት መታየት ያለበት በክልሉ በሚገኝ ፍርድ ቤት ነው” የሚል ነበር። አቤቱታው የቀረበለት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፤ የተከሳሽ ጠበቆችን እና የዐቃቤ ሕግን መከራከሪያ በጽሁፍ መቀበሉን የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ሃፍቶም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ይሁንና በዛሬው የችሎት ውሎ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚጠበቀው ውጤት ባለመቅረቡ ምክንያት፤ ችሎቱ ለሚያዚያ 10፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃው ገልጸዋል። የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ፣ የቀድሞው የፌደራል የገንዘብ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም እና የፓርላማ አባል የነበሩት ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፤ በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ችሎት ከቀረቡ ተከሳሾች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁንና ተከሳሾቹም ሆነ ጠበቆቻቸው በችሎት በነበሩበት ወቅት፤ ዛሬ ይፋ ስለተደረገው የህወሓት አመራሮች ክስ መቋረጥ የሚያውቁት ነገር እንዳልነበር ጠበቃቸው አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]