የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ተቋምን ለስድስት ዓመት ገደማ የመሩት አቶ ሮባ መገርሳ ከኃላፊነት ተነሱ

በአማኑኤል ይልቃል

በኢትዮጵያ ብቸኛ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ለሆነው፤ ለመንግስታዊው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ተቋም አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተሾመ። ዶ/ር በሪሶ አመሎ፤ ተቋሙን ስድስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የመሩትን አቶ ሮባ መገርሳን በመተካት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ትላንት ሐሙስ መጋቢት 21፤ 2015 ነው። 

በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የሚመራው የተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ በትላንትናው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ፤ የዶ/ር በሪሶን ሹመት ማጽደቁን የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ እና አዲሱ ተሿሚ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ከ18 ዓመታት በላይ ያገለገሉት አቶ ሮባ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አረጋግጠዋል።

እስከ ትላንት ድረስ ተቋሙን በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ሮባ፤ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በተቋሙ በተደረገው “ሽግሽግ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በተቋሙ ያለኝ “የአገልግሎት ጊዜዬን ጨርሻለሁ” ያሉት ተሰናባቹ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ ቀጣይ ማረፊያቸውን የት እንደሆነ እስካሁን እንዳላወቁ አስረድተዋል። 

በቀድሞው የባሕርና ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት ውስጥ “ለረጅም ጊዜ” የሰሩት አቶ ሮባ፣ በኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ውስጥ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍን ሲመሩ ቆይተዋል። ማልታ ከሚገኘው የዓለም አቀፍ ማሪታይም ህግ ኢንስቲትዩት “በማሪታይም ህግ” ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት አቶ ሮባ፤ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው እስከተሾሙት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር በመሆን በአመራርነት ሰርተዋል። 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት አቶ ሮባ፤ በዓለም አቀፍ ባህሮች እና በሀገር ውስጥ የውሃ አካላት ላይ ትራንስፖርት የመስጠት ኃላፊነት ያለበትን መንግስታዊ ድርጅት የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት በግንቦት 2009 ዓ.ም ነበር። የወደብ ይዞታዎችን የማልማት፣ ማስተዳደር እና አገልግሎት የመስጠት ስልጣን ያለው ይህ ተቋም፤ ስያሜውን ወደ “የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ” የቀየረው ከሁለት ወር በፊት ነው። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት “የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት” በሚል መጠሪያ ተቋሙ እንዲመሰረት ውሳኔ ሲያሳልፍ፤ ሶስት የመንግስት ድርጅቶችን በአንድ ላይ በማዋሃድ ነበር። አሁን ባለው ተቋም ስር እንዲጠቃለሉ የተደረጉት ሶስቱ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት አክስዮን ማህበር፣ የባሕርና ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም የደረቅ ወደብ አገልግሎት ድርጅት ናቸው። 

ለኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድ ቁልፍ የሆነውን ይህን ተቋም እንዲመሩ በትላንትናው ዕለት የተሾሙት ዶ/ር በሪሶ፤ በቻይና ሀገር ሲከታተሉ የቆዩትን የዶክትሬት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በቅርቡ ነው። ዶ/ር በሪሶ ቤጂንግ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍ ግነኙነት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከማግኘታቸው አስቀድሞ፤ አሁን ከተሾሙበት መስሪያ ቤት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ባለው በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል።

አዲሱ ተሿሚ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪ ያገኙት በ2005 ዓ.ም ነበር። ዶ/ር በሪሶ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው አራት ዓመት አስቀድሞ፤ በሻሸመኔ ከተማ አቅራቢያ ኩየራ ከሚገኘው የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ በማህበረሰብ ልማት እና አመራር የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸው ይዘዋል። አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ በተማሩበት ምዕራብ አርሲ ዞን ጨምሮ፤ በኦሮሚያ ክልል በዞን እና የከተማ መዋቅሮች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሰርተዋል። 

በምዕራብ አርሲ ዞን ደግሞ የትራንስፖርት ቢሮን ምክትል ኃላፊ በመሆን ያገለገሉት ዶ/ር በሪሶ፤ በሻሸመኔ ከተማ የህዝብ ግንኙነት ቢሮንም መርተዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የሰሩት ዶ/ር በሪሶ፤ በ2009 ዓ.ም የአምቦ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል። አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ “ሲንቄ” በሚል መጠሪያ ወደ ባንክነት ባደገው የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ውስጥም፤ ከምስረታው ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሰርተዋል። ዶ/ር በሪሶ ወደ ቻይና ለትምህርት እስከሚሄዱ ድረስ፤ በኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማት ቢሮ በአማካሪነት አገልግለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)