የፌደራል መንግስት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማ መላክ ሊጀምር ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የፌደራል መንግስት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማ መልቀቅ እንደሚጀምር የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ። ለክልሉ የሚለቀቀው በጀት፤ ለሌሎች ክልሎች እንደሚደረገው ሁሉ በወራት ተከፋፍሎ የሚላክ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። 

ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ይህን የተናገሩት፤ ለመንግስት ቅርበት ካለው ፋና ቴሌቪዥን ጋር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ነው። የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል በጀት ለማስተላለፍ ከስምምነት ላይ መድረሱን በተመለከተ አቶ ጌታቸው ረዳ ከቀናት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የሰጡትን ቃል፤ ሚኒስትር ዲኤታው ትላንት አርብ መጋቢት 22፤ 2015 ምሽት በተሰራጨው ቃለ ምልልሳቸው አረጋግጠዋል። 

ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት አቶ ጌታቸው፤ የፌደራል መንግስት በጀት መፍቀዱን፤ ሆኖም የገንዘብ መጠኑን በተመለከተ ግን “ገና እንነጋገራለን” ማለታቸው ይታወሳል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው በበኩላቸው፤ የትግራይ ክልል በጀት “የሚታወቅ” መሆኑን ገልጸዋል። 

የፌደራል መንግስት የ2015 ዓመትን በጀት ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ሲያጸድቅ፤ ለትግራይ ክልል 12.42 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ መመደቡን ይፋ አድርጎ ነበር። ዶ/ር እዮብ በፋና ቴሌቪዥን ቃለ ምልልሳቸው፤ ከዚሁ ጋር የተቀራረበ ቁጥር ጠርተዋል። የትግራይ ክልል ከዚህም በተጨማሪ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚውል 844.2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ከመንግስት ግምጃ ቤት እንደሚያገኝ በፌደራል በጀት ላይ ተመላክቶ ነበር። 

ይህ የገንዘብ መጠን ከጸደቀ ከአራት ወራት በኋላ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት፤ የትግራይ ክልል በጀት የሚለቀቅለት ጊዜያዊ አስተዳደር ሲያቋቁም መሆኑ ተገልጾ ነበር። የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እስኪቋቋም የበጀት ድጎማ ሳይለቅቅ ቢቆይም፤ በክልሉ ውስጥ ያሉ የፌደራል ተቋማትን ግን አስቀድሞ “ወደ ስራ ማስገባቱን” ዶ/ር እዮብ ተናግረዋል። ለዚህም በምሳሌነት የጠቀሱት የመብራት እና የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ነው። 

በትግራይ ክልል የሚገኙት የመቐለ፣ አክሱም እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች፤ ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈያ እና የአንድ ወር የስራ ማስኬያጃ በጀት ከገንዘብ ሚኒስቴር እንደተላለፈላቸው ከሁለት ሳምንት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀው ነበር። ዩኒቨርስቲዎቹ በጀቱ ወደ ባንክ ሂሳባቸው ከገባ በኋላ፤ የሶስት ወራት ውዝፍ ደመወዝ ለሰራተኞቻቸው መክፈላቸውን ገልጸዋል። በትምህርት ሚኒስቴር ስር የሚገኙት ሶስቱ ዩኒቨርስቲዎች፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ለ20 ወራት ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ ሳይከፍሉ ቆይተዋል። 

የትግራይ ክልል መንግስት ተቀጣሪ የነበሩ ሰራተኞች፤ በተመሳሳይ ምክንያት ለበርካታ ወራት ደመወዝ ሳያገኙ በመቆየታቸው “ለከፋ ችግር” ተዳርገዋል። የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል የሚሰጥ የበጀት ድጎማን ያቋረጠው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመስከረም 2013 ባስተላለፈው ውሳኔን መሰረት በማድረግ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ማቋረጥ ውሳኔን ያስተላለፈው፤ የትግራይ ክልል ከፌደራል መንግስት እውቅና ውጭ “ኢ-ህገ መንግስታዊ ምርጫ አካሄዷል” በሚል ነበር። 

ላለፉት ሁለት ዓመታት ለክልሉ መሰጠት የነበረበት እና በውዝፍ የቀረውን በጀት በተመለከተ፤ እስካሁን ውይይት አለመካሄዱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ለፋና ቴሌቪዥን ተናግረዋል። “ወደ ኋላ ያለውን፤ ‘ምን አቅም አለን? ምንድነው ፍላጎቱ? የሚለው ብዙ ውይይት ገና ይጠይቃል። እዚያ ላይ አልደረሰንም” ብለዋል ዶ/ር እዮብ። 

“ብዙ ጥያቄ አለ። የፈረሱ አሉ። ‘እነዚህን ነገሮች እንዴት እንገነባ?’ የሚል ከሁሉም በግጭት ከተጎዱ አካባቢዎች ይነሳል። ለዚህ ደግሞ የመልሶ ግንባታ እቅድ እያዘጋጀን ነው። በዚያ ውስጥ የምንመልሰው ይሆናል” ሲሉም የፌደራል መንግስት ለዚህ ጉዳይ በመፍትሔነት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።የፌደራል መንግስት አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው “ክልሉን ወደ ስራ ማስገባት” መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ብዙ ጥያቄ አለ። የፈረሱ አሉ። ‘እነዚህን ነገሮች እንዴት እንገነባ?’ የሚል ከሁሉም በግጭት ከተጎዱ አካባቢዎች ይነሳል። ለዚህ ደግሞ የመልሶ ግንባታ እቅድ እያዘጋጀን ነው። በዚያ ውስጥ የምንመልሰው ይሆናል”

ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ – የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ

በአዲስ አበባ የሚገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች “ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ይገባሉ” ያሉት ዶ/ር እዮብ፤ ይህን ተከትሎም የፌደራል መንግስት በጀት የመልቀቅ ስራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል። የበጀት ማስተላለፍ ስራው ግን ልክ ለሌሎች ክልሎች እንደሚደረገው፤ የትግራይ ክልልን የየወሩን ድርሻ በመላክ የሚተገበር እንደሆነ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[የ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]