በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በ18 ወረዳዎች የኮሌራ ወረረሽኝ እንዳለ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ  

በሃሚድ አወል

በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በአምስት ወረዳዎች የተቀሰቀሰውን የኮሌራ ወረረሽኝ መቆጠጣጠር ቢቻልም፤ ወረርሽኙ አሁንም በ18 ወረዳዎች መኖሩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የኩፍኝ ወረርሽኝ እና የወባ በሽታም በተለያዩ ክልሎች መከሰታቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከትላንት በስቲያ አርብ መጋቢት 22፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ገልጿል። 

የጤና ሚኒስቴር የአርብ ዕለት መግለጫ፤ ለድርቅ እና ተያያዥ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች እየተሰጡ ባሉ ምላሾች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህ መግለጫው ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ፤ የኮሌራ ወረርሽኝ በኦሮሚያ ክልል አራት ዞኖች በሚገኙ 18 ወረዳዎች እና በሶማሌ ክልል አራት ወረዳዎች መከሰቱን ጠቁሟል። ከእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ በአምስት ወረዳዎች ወረርሽኙን መቆጣጠር መቻሉን ገልጿል።  

የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው በሁሉም ወረዳዎች 23 ጊዜያዊ የማከሚያ ማዕከላት መቋቋማቸውን ያመለከተው ሚኒስቴሩ፤ “የህክምና ግብዓቶች ለማዕከላቱ በማሰራጨት ተገቢው አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ” ብሏል። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በተወሰደው እርምጃም፤ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች “ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች” የኮሌራ ክትባት መስጠቱን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ወረርሽኙ ለተከሰተባቸው እና ለአጎራባች ወረዳዎች የሚሆን 1.2 ሚሊዮን ክትባት ለማግኘት ለዓለም የጤና ድርጅት ጥያቄ መቅረቡን አክሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN OCHA) ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ባወጣው ሪፖርት፤ የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው ወረዳዎች “ወደ 3.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፍተኛ ስጋት ተጋልጠዋል” ብሎ ነበር። በማስተባበሪያ ቢሮው ሪፖርት መሰረት፤ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ 2,276 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ ሲጠቁ፤ 50 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከኮሌራ ወረርሽኝ በተጨማሪ የኩፍኝ በሽታ ወረረሽኝም ለሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። በኩፍኝ በሽታ ባለፉት 18 ወራት 153 ሰዎች መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር ባለፈው አርብ ባወጣው መግለጫው አስታውቋል። በእነዚህ ወራት 14,775 ሰዎች በኩፍኝ በሽታ መጠቃታቸው ሪፖርት መደረጉን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አክሏል። በስድስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ ከተመዘገቡ የኩፍኝ በሽታ ህመምተኞች ውስጥ፤ 14,334ቱ ማገገማቸውም ተመልክቷል። በእነዚህ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ያሉ ህምመተኞች ብዛት 288 እንደሆነ መግለጫው ጠቁሟል።

ከኮሌራ ወረርሽኝ እና ከኩፍኝ በሽታ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የወባ በሽታ መጨመር እንደታየ የጤና ሚኒስቴር በዚሁ መግለጫው አስታውቋል። “በሀገር አቀፍ ደረጃ፤ ካለፈው ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር መጨመር በተለያዩ ክልሎች ታይቷል” ሲል ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስፍሯል። ከአፋር እና ሐረሪ ክልሎች በስተቀር፤ በወባ በሽታ የተጠቁ ህመምተኞች ቁጥር “ካለፉት አምስት ዓመታት ጋር ሲነጻጻር ከተለመደው በተለየ ሁኔታ ከፍ ብሎ እንደነበር” የቅኝት መረጃዎችን ጠቅሶ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እና ስርጭቱን ለመግታት 19.6 ሚሊዮን አጎበር ተዘጋጅቶ ወደ የአካባቢው መላኩን እና ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ መሰራጨቱን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም በቂ የጸረ ወባ መድኃኒቶች በመሰራጨታቸው፣ የወረርሽኝ ስጋት ተግባቦት እና የማህበረሰብ ንቅናቄ በተለያዩ ደረጃዎች በመካሄዱ፤ “በአሁኑ ወቅት የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረባቸው ወረዳዎች ለመቆጣጠር ተችሏል” ብሏል ሚኒስቴሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)