የጋምቤላ ክልል መንግስት “ጋነግ” ከተባለው ታጣቂ ቡድን ጋር የሰላም ንግግር መጀመሩን ገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

የጋምቤላ ክልል መንግስት፤ ከአማጺው የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ጋር የሰላም ንግግር ማድረግ መጀመሩን አራት የክልሉ ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የሰላም ንግግሩ፤ በደቡብ ሱዳን ጁባ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ሁለት ጊዜ መደረጉ ተገልጿል።

ከሐምሌ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትጥቅ ትግል የገባው ጋነግ፤ በጋምቤላ ክልል የቀድሞ ባለስልጣናት በነበሩ ግለሰቦች የሚመራ ነው። ታጣቂ ቡድኑ “በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል ጸብ እንዲፈጠር የሚሰራ” መሆኑን የጋምቤላ ክልል መንግስት ከዚህ ቀደም ባወጣቸው መግለጫው ሲወንጅል ቆይቷል። ጋነግ የብዙዎች ትኩረት ውስጥ የገባው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ፤ ራሱን የ“ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” በማለት ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር በመሆን በጋምቤላ ዋና ከተማ ላይ ጥቃት ከከፈተ በኋላ ነበር። 

ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች በከፈቱት በዚሁ ጥቃት፤ የጋምቤላ ከተማን ለአጭር ጊዜም ቢሆን በከፊል ተቆጣጥረው እንደነበር ይታወሳል። ታጣቂዎቹ ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ለሰዓታት ከተደረገ የተኩስ ልውውጥ በኋላ የጋምቤላ ከተማ ለቅቀው መውጣታቸውም አይዘነጋም። ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች የጋምቤላ ከተማን በተቆጠጠሩበት ዕለት ሰባት ሲቪል ሰዎችን እንደገደሉ እና በሌሎች ላይ የአካል ጉዳት እና ዝርፊያ መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመስከረም 2015 ባወጣው ሪፖርት አስታውቆ ነበር። 

ከሰኔው ጥቃት በኋላ ስሙ ጉልህ ተነስቶ የማያውቀው ጋነግ ከጋምቤላ ክልል መንግስት ጋር የሰላም ንግግር ማድረግ የጀመረው፤ አማጺው ቡድን “ባቀረበው ጥያቄ” እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የክልሉ ባለስልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ታጣቂ ቡድኑ፤ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ያቀረበውን ይህን የሰላም ጥሪ ተከትሎ፤ የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናትን እና የመከላከያ ሰራዊት የጦር መኮንኖችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ባለፈው የካቲት ወር ላይ ወደ ስፍራው ማቅናቱንም አክለዋል።

በወቅቱ ወደ ጁባ ከተጓዙት መካከል የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ እንዲሁም የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ይገኙበታል። በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ በተደረገው በዚህ የሰላም ንግግር፤ ታጣቂ ቡድኑ በሰላም ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ስምምነት ላይ መድረሱን እኚሁ የክልሉ ባለስልጣን አስረድተዋል። በሰላም ንግግሩ የተሳተፉ የታጣቂ ቡድኑ ተወካዮች፤ የውይይቱን ውጤት በተመለከተ ከአባላቶቻቸው ጋር ከተወያዩ በኋላ ፍላጎቶቻቸውን ለመንግስት እንደሚያቀርቡ ገልጸው እንደነበርም ጠቁመዋል።  

የጋነግ ተወካዮች እና የጋምቤላ ክልል የስራ ኃላፊዎች በጁባ የሰላም ንግግር አድርገው እንደነበር የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸንኮት ቾድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “ባለፈው ጁባ አመቻችተው አንድ መድረክ ተፈጥሯል። አዲስ አበባ አንድ መድረክ እንደገና ተፈጥሯል” ሲሉም የሰላም ንግግሩ በሀገር ውስጥ መቀጠሉን አስረድተዋል። 

የጋምቤላ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸንኮት ቾድ፤ የክልሉ ባለስልጣናት እና የጋነግ ተወካዮች በደቡብ ሱዳን ጁባ እና በአዲስ አበባ የሰላም ንግግር ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል | ፎቶ፦ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የተጀመረው የሰላም ንግግር በአሁኑ ወቅት እየተመራ ያለው፤ የፌደራል መንግስት በክልሉ ውስጥ ባዋቀረው ኮሚቴ መሆኑንም አስታውቀዋል። በዚህ የሰላም ኮሚቴ ውስጥ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንን መካተታቸውን የገለጹት አቶ ቸንኮት፤ የፌደራሉ መንግስት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር በሚደረገው ንግግር ላይ ተሳታፊ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በአዲስ አበባ በተደረገው የሰላም ንግግር ላይ የተገኙት የጋነግ ተወካዮች፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርነትን የመሰሉ ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ላይ እንዲሾሙ ጥያቄ ማቅረባቸውን ስለ ጉዳዩ ዕውቅት ያላቸው የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይሁንና “መንግስት በሚያስፈልገው ቦታ ላይ ነው የሚያስቀምጣችሁ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው እና ተወካዮቹ በዚህ እንደተስማሙ ገልጸዋል።

የታጣቂ ቡድኑን አባላት በተመለከተ የተደረሰውን ስምምነት ሲያብራሩም፤ “እንደየችሎታቸው ምድብ ስራ ይሰጣቸዋል። ተማሪዎችም ከሆኑ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ፣ ሰራተኞችም ከሆኑ ወደ ስራቸው [ይገባሉ]። ስራ የመስራት አቅሙ ከሌላቸው በማህበር ተደራጅተው ራሳቸውን የሚችሉበት መንገድ ይፈጠራል” ብለዋል። የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች እና አባላት “መቼ ወደ ሀገር ውስጥ ይመለሳሉ?” የሚለው ጥያቄ ግን እስካሁን በግልጽ እንዳልታወቀ አክለዋል።

የጋነግ ታጣቂዎች ወደ ጋምቤላ ከተማ ገና አለመግባታቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ተናግረዋል

የጋምቤላ ክልል መንግስት ለታጣቂ ቡድኑ አቀባበል የሚያደርገው፤ ጋነግ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ለፌደራሉ መንግስት ሪፖርት ካደረገ በኋላ መሆኑን እኚሁ የክልሉ የስራ ኃላፊ ገልጸዋል። የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ፤ የጋነግ “ታጋይ” የተባሉት ወደ ሀገር ውስጥ አለመግባታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም የክልሉ መንግስት “በሰፈር ውስጥ” የሚንቀሳቀሱ የጋነግ አባላትን፤ ወደ ስልጠና ካምፕ ማስገባቱን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)