የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው፤ በነገው የፓርላማ ስብሰባ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ ነው 

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃነመስቀል ዋጋሪ እና ምክትላቸው ወ/ሮ ተናኘ ጥላሁን፤ ነገ ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 በሚካሄደው የፓርላማ ስብሰባ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በምትካቸው አዳዲስ ኃላፊዎች ሊሾሙ ነው። አቶ ብርሃነመስቀል “በገዛ ፈቃዳቸው” የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ወይዘሮ ተናኘ ጥላሁን በበኩላቸው “በጤንነት ምክንያት” ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ በሂደት ላይ መሆናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ሁለቱ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው የሚነሱት፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳት እና ምክትላቸው ስራ መልቀቃቸውን ተከትሎ አዳዲስ ተሿሚዎች ቦታውን ከተረከቡ ከሁለት ወራት በኋላ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ባካሄደው ስብሰባ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳት በነበሩት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ምትክ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ምህረትን መተካቱ ይታወሳል። 

ፓርላማው በዚሁ ስብሰባው፤ እንደ ወ/ሮ መአዛ ሁሉ ከኃላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁትን አቶ ሰለሞን አረዳን እንዲተኩ ወ/ሮ አበባ እምቢአለን መሾሙ አይዘነጋም። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ በተመሳሳይ መልኩ “በገዛ ፍቃዳቸው” የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን በተናገሩት፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ምትክ አዲስ ኃላፊ እንደሚሾም አስታውቋል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነት የሰሩት አቶ ብርሃነመስቀል፤ የስራ መልቂቂያ ያስገቡት ከሁለት ሳምንት በፊት መጋቢት 12፤ 2015 መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። አቶ ብርሃነመስቀል ዛሬ ከሰዓት በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ በሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው ቢሯቸው፤ “የወረቀት ስራዎችን ለመጨረስ” ተገኝተው እንደነበር የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።

ፎቶዎች፦ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

ተሰናባቹ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወደዚህ ኃላፊነት ቦታ ከመምታጣቸው በፊት፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነትን ከአቶ በላቸው አኑቺሳ ተረክበው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ብርሃነመስቀል፤ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ፍርድ ቤቶች በዳኝነትም አገልግለዋል።

ከአቶ ብርሃነመስቀል ጋር በአንድ ላይ ሹመታቸውን ካገኙ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች መካከል፤ በነገው ዕለት ኃላፊነታቸውን የሚያስረክቡት ወ/ሮ ተናኘ ጥላሁን ናቸው። ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት ወ/ሮ ተናኜ፤ በእርሳቸው ቦታ መስሪያ ቤታቸው ሌላ ሰው ሊተካ እንደሚችል አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)