⚫ በሶማሌ ክልል በዳኝነት ያገለገሉት ዘሃራ ኡመር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነዋል
በአማኑኤል ይልቃል እና በሃሚድ አወል
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ለሶስት ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሰሩት ሌሊሴ ደሳለኝ፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ። በሶማሌ ክልል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ያገለገሉት ዘሃራ ኡመር አሊ ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል።
የሁለቱን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኃላፊዎች ሹመት፤ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ድምጸ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። የተወካዮች ምክር ቤት የሁለቱ ዳኞች ሹመት የቀረበለት፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃነመስቀል ዋጋሪ እና ምክትላቸው ወ/ሮ ተናኘ ጥላሁን “በፍቃዳቸው የስራ መልቀቂያ በማስገባታቸው” ነው።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን የመምራት ኃላፊነት ዛሬ የተረከቡት ሌሊሴ ደሳለኝ፤ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ ለ20 ዓመት ገደማ ያገለገሉ ናቸው። በ1994 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ የያዙት ሌሊሴ፤ በትራንስፎርሜሽናል አመራር እና ለውጥ ትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ህግ ትምህርትን እየተከታተሉ ነው።
ሌሊሴ፤ የዳኝነት ስራቸውን የጀመሩት በ1994 ዓ.ም በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኛ በመሆን ነው። ከ1995 እስከ 1999 ባሉት አመታት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ እና አዳማ ልዩ ዞኖች ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ዳኛ ሆነው ሰርተዋል። በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውስጥ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት (acting president) በመሆን ወደ አመራርነት የመጡት ሌሊሴ፤ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው በኃላፊነት ሰርተዋል።
አዲሷ ተሿሚ ከዚህ በኋላ ቀጣይ መዳረሻቸውን ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ነበር። በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም ዳኛ ሆነው የሰሩት ሌሊሴ፤ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋውረው ለአንድ ዓመት ገደማ አገልግለዋል። ከጥር 2008 ዓ.ም ጀምሮ አሁን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተሾሙበትን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ተሹመው ነበር። ሌሊሴ በዚህ የኃላፊነት ቦታቸው ለሶስት ዓመት ከአምስት ወር ገደማ ቆይተዋል። የዛሬውን ሹመት እስካገኙበት ጊዜ ድረስ ደግሞ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ ዳኛ ሆነው እየሰሩ ነበር።
ፓርላማው በዛሬው ውሎ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነት ሹመታቸውንው ያጸደቀላቸው ዘሃራ ኡመር፤ አብዛኛውን የዳኝነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ ነው። የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የህግ ምሩቋ ዘሃራ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት በ1992 ዓ.ም ነው። በዚሁ ዓመት በሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ የወንጀል ችሎት ዳኛ ሆነው መስራት የጀመሩት ዘሃራ፤ ለአራት ዓመት በዚሁ ስራ ቆይተዋል።
እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ በፍትሐ ብሔር እና በሰበር ሰሚ ችሎቶች ውስጥ በዳኝነት አገልግለዋል። ዘሃራ ከዳኝነት ስራ ወጥተው ጠበቃ በመሆንም ለአምስት ዓመታት ሰርተዋል። አዲሷ ተሿሚ የፌደራል የዳኝነት ኃላፊነት ሹመትን ከማግኘታቸው አስቀድሞ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሶማሌ ክልል የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)