የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት “ደረጃ በደረጃ እንደሚያስተካክል” ጆሴፕ ቦሬል አስታወቁ

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን ግጭት አፈታት ሂደት እየተከታተለ እንደሚገኝ የህብረቱ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ተናገሩ። ስፔናዊው የአውሮፓ ከፍተኛ ዲፕሎማት፤ “ግንኙነታችንን ወደ ነበረበት የምንመልሰው በሂደት እና ደረጃ በደረጃ ነው” ሲሉ ለኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እና ለትግራይ ባለስልጣናት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩ የቆዩት ቦሬል፤ በፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት የቆመውን ግጭት አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ቦሬል ይህንን መግለጫ የሰጡት፤ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በቤልጅየም ዋና ከተማ ብራስልስ ካደረጉት ውይይት በኋላ ነው። 

ሁለቱ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ባደረጉት በዚህ ውይይት፤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ሂደት መነጋገሪያ ነበሩ። የኢትዮጵያ ጦርነት “ትልቅ ቀውስ ነበር” ያሉት ቦሬል፤ “አሁን እንደ ዕድል ሆኖ ነገሮች ወደ መፍትሄው እየሄዱ ነው” ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል።   

ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከተለው ይህ ጦርነት፤ በፕሪቶሪያ በተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት መፍትሔ ማግኘቱ “በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት በጎ ዜናዎች አንዱ” እንደሆነ ቦሬል እምነታቸውን ገልጸዋል። ቦሬል ታይቷል ያሉትን አዎንታዊ ለውጥ ዘላቂ ለማድረግ “የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራታቸውን መቀጠላቸው ጠቃሚ” እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል። “ለኢትዮጵያ መንግስት እና ለትግራዮች የምናስተላልፈው መልዕክት፤ የግጭቱን አፈታት እየተከታተልን እንደሆነ እንዲረዱ ነው” ሲሉ ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረትም ጠቆም አድርገዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለሁለት ዓመታት በተደረገው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት፤ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ እና የልማት እገዛ  ማገዱ ይታወሳል። ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ የጥንቃቄ አካሄድ እንደሚከተል ቦሬል በዛሬው መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል። የአውሮፓ ህብረት የውጪ ግንኙነት ኃላፊ “ግንኙነታችንን ወደ መደበኛነት የምንመልሰው በሂደት እና ደረጃ በደረጃ ብቻ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከአውሮፓ ህብረት ጋር “በቅንጅት እና በትብብር የምትሰራው ስራ ለውጥ” ይመጣባቸዋል ካሏቸው ቦታዎች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አስታውቀዋል። ብሊንከን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ “ፈታኝ” ሲሉ የጠሯቸው፤   ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና መካከለኛው ምስራቅን ነው። እነዚህን ቦታዎች በቅርቡ መጎብኘታቸው የጠቀሱት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “በእነዚህ ሁሉ አካባቢዎች፤ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው ቅንጅት በጣም ጥሩ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

አንቶኒ ብሊንከን በመጋቢት የመጀመሪያ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከተመለሱ በኋላ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በፕሪቶሪያ የተፈራረሙት ግጭት የማቆም ስምምነት አተገባበር ከፍተኛ ፍጥነት አሳይቷል። ከእርሳቸው ጉብኝት አንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ፤ የሰላም ስምምነቱን በደቡብ አፍሪካ የተፈራረመው ህወሓት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሽብርተኝነት ዝርዝር ተሰርዟል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ሲመጡ ያገኟቸው አቶ ጌታቸው ረዳም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተሹመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)