አብን፤ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ለማስፈታት የተላለፈውን ውሳኔ እንደሚቃወም አስታወቀ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ለማስፈታት በገዢው ፓርቲ ተላልፏል ያለውን ውሳኔ እንደሚቃወም አስታወቀ። ውሳኔው፤ የአማራ ህዝብን  “ያለ ተከላካይ፣ ለዳግም ወረራ እና ጥቃት የሚዳርግ ነው” ሲል ፓርቲው ነቅፏል። 

አብን በጉዳዩ ላይ ያለውን ተቃውሞውን ያስታወቀው፤ ወቅታዊ ጉዳይን በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት ያህል አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የአብን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከተወያየባቸው “አንኳር ጉዳዮች” መካከል አንዱ የልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታትን የተመለከተው አንዱ እንደሆነ ገልጿል።

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “የክልል ልዩ ኃይሎችን በሚመለከት” ውሳኔ ማሳለፉን በመግለጫው የጠቀሰው አብን፤ የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ “የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን ገምግሜያለሁ” ብሏል። ይህ ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ፤ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌለውም ፓርቲው በመግለጫው አስፍሯል። 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት፤ “በቂ የሽግግር ጊዜ ከተሰጠ በኋላ ማስተካከል ይገባል” የሚል መርህን የሚያራምድ ቢሆንም፤ ገዢው ፓርቲ አሁን ያሳለፈው ውሳኔ ግን “ወቅቱን ያልጠበቀ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” ሲል ተችቶታል። ከዚህ በተጨማሪ ውሳኔው ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እና የህብረተሰብ ክፍሎችን፤ “ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት እና አደጋ የሚዳርግ ነው” ሲል አብን ስጋቱን ገልጿል።

በየክልሉ የተደራጁ ልዩ ኃይሎች “አፈጣጠር እና አደረጃጀት” የራሱ የሆነ ችግር እንዳለበት በመግለጫው የጠቆመው አብን፤ “አሁን ባለው ተጨባጭ እና ነባራዊ ሁኔታ” የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ማፍረስ ተገቢ አለመሆኑን አመልክቷል። “የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ማፍረስ… የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ በመሆኑ አብን አጥብቆ የሚቃወመው ውሳኔ ነው” ሲል ፓርቲው በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም ይፋ አድርጓል። 

በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት “በአግባቡ ተግባራዊ አልተደረገም” ያለው ፓርቲው፤ በዚህ ሁኔታ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት ተገቢ አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል። አብን፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት በተባለው መሰረት ላለመተግበሩ አንዱ ማሳያ በማለት በመግለጫው የጠቀሰው “የህወሓት ኃይሎችን ትጥቅ አለመፍታት ነው”። እንዲያውም ህወሓት “ተጨማሪ ኃይል እያሰለጠነ እና እያደራጀ ይገኛል” ሲል አብን ወንጅሏል። 

“በአሁኑ ሰዓት የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት፤ ክልሉን ላልተጠበቀ ስርዓት- አልበኝነት እና ለሽብርተኛ ኃይሎች መፈንጫነት የሚያመቻች በመሆኑ፤ የገዥው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ የወሰነው ውሳኔ ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ነው”

– የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

አብን የሰላም ስምምነቱ በአግባቡ ተግባራዊ ላለመደረጉ በሁለተኛነት የጠቀሰው ምሳሌ፤ “የሀገር መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክልልን ጸጥታ [ማስከበር] አልተረከበም” የሚል ነው። “መንግስት የጸጥታ ማረጋገጥ ስራውን ባግባቡ ስላልተወጣ የደህንነት ማረጋገጫ እና ዋስትና መስጠት የሚችልበት ሁኔታ አልፈጠረም” ያለው ፓርቲው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ያስተላለፈው ውሳኔ “ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ ነው” ሲል ተችቷል።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት “ወደ ጎን በተገፋበት” እና ህወሓት “ለሌላ ዙር ጦርነት በግልጽ ዝግጅት እያደረገ ባለበት” በዚህ ጊዜ፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፍታ ማለት “የአማራ ህዝብን ያለ ተከላካይ ለዳግም ወረራ እና ጥቃት የሚዳርግ” በመሆኑ የገዢው ፓርቲ ውሳኔ እንደሚቃወም አብን አስታውቋል። “በአሁኑ ሰዓት የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት፤ ክልሉን ላልተጠበቀ ስርዓት- አልበኝነት እና ለሽብርተኛ ኃይሎች መፈንጫነት የሚያመቻች በመሆኑ፤ የገዥውን ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ የወሰነው ውሳኔ ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ነው” ሲልም አብን በመግለጫው አስፍሯል። 

የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ጨምሮ አጠቃላይ “የፌዴሬሽኑን አወቃቀር” በሚመለከት ስምምነት ሊደረስበት ይገባ የነበረው፤ በመጪው ግንቦት ወር ሊደረግ በታሰበው “የብሔራዊ ምክክር መድረክ” ላይ እንደሆነ ፓርቲው ጠቁሟል። በዚህ ጉዳይ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ “በጥድፊያ” ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያደርገው ሙከራ፤ “ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል” መሆኑን አብን በመግለጫው አስጠንቅቋል። የአማራ ክልል መንግስትም በገዢው ፓርቲ የሚተላለፉ ይህን መሰል ውሳኔዎችን “እንዳይተገበር የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለበት” መሆኑን አብን አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]