በሃሚድ አወል
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት በአምስት እጥፍ ሊያድግ እንደሚችል የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ሀብታሙ ተገኝ ተናገሩ። ህገ ወጥ የወርቅ ማውጣት እና ንግድን ለመቆጣጠር “የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት” እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
አቶ ሀብታሙ ይህን የገለጹት በማዕድን ዘርፍ የሚታዩ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 27፤ 2015 በተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደ ውይይት ላይ ነው። በፓርላማው የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው በዚህ ውይይት ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከወርቅ ምርት ጋር የተያያዙ ነበሩ።
አቶ ሀብተማሪያም መኮንን የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፤ “በባህላዊ መንገድ ተመርቶ የሚፈለገውን ያህል ወደ ብሔራዊ ባንክ እየቀረበ አይደለም። ኮንትሮባንድ ይበዛበታል ስርቆት ይበዛበታል። ይህንን እንዴት አድርገን ማሻሻል አለብን?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወ/ሮ ሐረገወይን ይመርም በተመሳሳይ ቋሚ ኮሚቴው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ያደረገውን የመስክ ምልከታ በአስረጂነት አንስተው፤ የህገ ወጥ የወርቅ ምርት “አሳሳቢ” መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሁ ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ “ከወርቅ አውጪ ማህበራት ውጪ፣ ‘ወርቅ አዘዋዋሪ ነን’ የሚሉ፣ ሚዛን ይዘው ወርቅ ሲሰበስቡ የሚውሉ አካላት አሉ” ሲሉ ሐረገወይን በዛሬው ውይይት ላይ ተናግረዋል። በቁጥር 29 ከሆኑት ከእነዚህ ወርቅ አዘዋዋሪዎች መካከል፤ ፈቃድ ማቅረብ የቻለው አንድ አዘዋዋሪ ብቻ መሆኑንም አክለዋል።
የማዕድን ሚኒስቴርን የመምራት ስልጣን ከአቶ ታከለ ኡማ ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ላይ የተከረቡት አቶ ሀብታሙ፤ የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት በአብዛኛው የባህላዊ እና ጥቃቅን እና አነስተኛ አምራቾች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገልጸዋል። “በጥቃቅን እና አነስተኛ ወርቅ እየተመረተ፤ የሀገርን የውጭ ምንዛሬ እና የወርቅ አቅርቦት ብዙም ማስኬድ አይቻልም” ሲሉም ዘርፉ ላይ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ላይ የሚሳተፉ “ብዙ ፋብሪካዎች ያስፈልጓታል” ያሉት የማዕድን ሚኒስትሩ፤ በዚህ ደረጃ ወርቅ ሊመረትባቸው የሚችሉ አምስት “ፕሮጀክቶች” መኖራቸውንም ለፓርላማ ኮሚቴው አባላቱ ገልጸዋል። ወርቅ በፋብሪካ ደረጃ ሊመረትባቸው ይችላሉ ተብለው በሚኒስትሩ የተጠቀሱት እነዚህ አካባቢዎች የሚገኙት፤ በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልል መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች በዚህ መልኩ ወርቅ ማምረት ሲጀምር የሚኖረውን ለውጥ አቶ ሀብታሙ ሲያስረዱ፤ “በፋብሪካ ደረጃ ብናመርት፤ የወርቅ ምርታችን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት፤ አምስት እጥፍ [ድረስ] ሊሄድ ይችላል” ብለዋል። “ከባንኮች ጋር ያለው ነገር ከተፈታ፣ የጸጥታ ሁኔታው ከተስተካከለ፣ ወርቅ ላይ ያለው ነገር በሚቀጥሉት ዓመታት በጉልህ መሻሻሎችን ያሳያል” ሲሉ የማዕድን ሚኒስትሩ ተስፋቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አጋርተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በ11 ወራት ውስጥ ካመረተችው 8.1 ቶን ወርቅ፤ 513 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘች የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ሊጠናቀቅ ሶስት ወራት ብቻ በቀሩት የዘንድሮው የ2015 በጀት ዓመት፤ ኢትዮጵያ ከወርቅ ምርት ለማግኘት ያቀደችው ገቢ 879.3 ሚሊዮን ዶላር ነው። ሀገሪቱ በግማሽ ዓመቱ ከወርቅ ኤክስፖርት ማግኘት የቻለችው ገቢ ግን 117.4 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ቀድሞው የማዕድን ሚኒስትር አቶ ታከለ ኡማ መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት “በከፍተኛ መጠን” መቀነሱን አስታውቆ ነበር። ሪፖርቱን ያቀረቡት የቀድሞው የባንኩ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ፤ ሀገሪቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለውጭ ገበያ ያቀረበችው የወርቅ መጠን ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
በወርቅ ምርት መጠን ላይ የታየው ማሽቆልቆል፤ ይህ የማዕድን ውጤት ለወትሮው በሀገሪቱ የወጪ ንግድ ላይ የነበረውን አበርክቶትም አሳጥቶታል። በባለፈው ዓመት የ11 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም፤ ወርቅ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድርሻ ይዞ ነበር። በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ግን ወቅር ይህን ድርሻውን ለአበባ ማስረከቡን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
የቀድሞዎቹ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እና የማዕድን ሚኒስትርም ሆኑ አዲሱ ተሿሚ አቶ ሀብታሙ፤ ለሀገሪቱ የወርቅ ምርት መቀነስ በምክንያትነት የሚነሷቸው የጸጥታ ችግር እና ህገ ወጥ ንግድን ነው። “ወርቅ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ከተወሰኑ ቦታዎች ውጭ በሙሉ በህገ ወጥ ታጣቂዎች፣ በታጠቁ፣ በሚያሸብሩ ኃይሎች የተያዙ ናቸው” ሲሉ አቶ ሀብታሙ በዛሬው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ውይይት ላይ ተናግረዋል። “እነዚህ ቦታዎች ላይ ጸጥታውን ማስከበር ያስፈልጋል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ የማዕድን ሀብቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት መሰማራቱን ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።
አዲሱ የማዕድን ሚኒስትር፤ የሕገ ወጥ ወርቅ ምርትን መቆጣጠርን በተመለከተ በመንግስት በኩል የተደረገውን ጥረትም በዛሬው ውይይት አስረድተዋል። ህገ ወጥ የወርቅ አምራቾችን ለመቆጣጠር በሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በኩል ስራዎች መጀመራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ግለሰቦቹ “ማን ናቸው? ማን ነው አብሯቸው የሚሰራው የሚለውን [ለማወቅ] አልተቻለም” ብለዋል። ለሕገ ወጥ የወርቅ ምርት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት “የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት” እንደሚያስፈልግም አቶ ሀብታሙ። ለዚህም መስሪያ ቤታቸው ከብሔራዊ ባንክ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)