ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የፓርላማ አባል ዛሬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

በሃሚድ አወል

በትላንትናው ዕለት ያለመከሰስ መብታቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተነሳው የፓርላማ አባል ዶ/ር ጫላ ዋታ፤ ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ዶ/ር ጫላ በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት በነበረው መደበኛ ስብሰባው የፓርላማ አባሉን የህግ ከለላ ያነሳው፤ ዶ/ር ጫላ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት “ከመንግስት ሕግ ውጪ” ግዢዎች እና የፋይናንስ አስተዳደር ጉድለቶችን ለመፈጸማቸው “በቂ አመላካች ሁኔታዎች አሉ” በሚል ነበር። ዶ/ር ጫላ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነታቸው የተነሱት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ከኃላፊነታቸው የተነሱት፤ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ካካሄደው የስራ ግምገማ በኋላ “በወሰደዉ አስተዳደራዊ እርምጃ መሰረት” መሆኑን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ከዘጠኝ ወር በፊት በተወሰደው በዚሁ አስተዳደራዊ እርምጃ፤ የዩኒቨርሲቲው ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶችም ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል። 

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የዩኒቨርሲቲውን የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ይፋ ካደረገ ከሶስት ወራት በኋላ ነው። በ40 ገጾች የተዘጋጀው የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ የሂሳብ ወጪ እና የግዢ ስርዓት ጉድለቶች እንዳሉበት ያመለከተ ነበር።

የዶ/ር ጫላ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማ ያቀረበው የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በዚሁ የኦዲት ግኝት ላይ በመመስረት ውሳኔውን እንዳዘጋጀ አስታውቆ ነበር። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ ትላንት ማክሰኞ ለፓርላማ ሲናገሩ “ለዚህ ጉዳይ ትልቁ መነሻ የኦዲት ግኝት ነው” ብለዋል። ይኸው የኦዲት ሪፖርት፤ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ሰብስቦ ማወራረድ የሚገባው 63 ሚሊዮን 421 ሺህ ብር ገደማ ገንዘብ አለመሰብሰቡን አመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ “ከአዋጅ እና ከመመሪያ ውጭ”፤ በ24.7 ሚሊዮን ብር የዕቃ እና አገልግሎት የቀጥታ ግዢ መፈጸሙን በሪፖርቱ ተገልጿል። ዩኒቨርሲቲው ለስራ ተቋራጮች የ5.8 ሚሊዮን ብር ክፍያ ቢፈጽምም፤ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ሳይቀበል በመቅረቱ “የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋጋጥ አለመቻሉን” በሪፖርቱ ሰፍሯል። 

የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ለተቋራጮች ከተገባው ውል በላይ፤ 21.1 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙም በፌደራል ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት ላይ ተቀምጧል። ክፍያው “ከደንብ እና መመሪያ ውጭ” በመከናወኑ የህግ ጥሰት ከማስከተሉ በተጨማሪ፤ “የመንግስት ውስን ሀብት አላግባብ እንዲወጣ ተደርጓል” ሲል ሪፖርቱ አብራርቷል። 

የፌደራል ኦዲተር መስሪያ ቤት ይህን ሪፖርት ለዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጀንበሩ አበበ እና ለምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር በወቅቱ ልኮ ነበር። የሪፖርቱ ዓላማ በኦዲት ወቅት የተገኙ “ድክመቶችን እና ግድፈቶችን” የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር አካላት “እንዲያውቁት እና ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ምላሽ እንዲሰጡበት ለማስቻል ነው” ሲልም መስሪያ ቤቱ በወቅቱ አስታውቋል።

ዶ/ር ጫላ ይህ የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተወካዮች ምክር ቤትን ተቀላቅለዋል። ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ምርጫ ክልልን ወክለው ወደ ፓርላማ የገቡት ዶ/ር ጫላ፤ የተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆናቸው በህግ ያገኙትን ያለመከሰስ መብት በትላንትናው ዕለት አጥተውታል። 

የተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የዶ/ር ጫላን ያለመከሰስ መብት ያነሳው በአብላጫ ድምጽ ነው። በትላንትናው ስብሰባ ላይ ከተገኙ 248 አባላት ውስጥ፣ ብቸኛ ድምጸ ተዐቅቦ ያስመዘገቡት ራሳቸው ዶ/ር ጫላ ዋታ ናቸው። ዶ/ር ጫላ የትላንትናው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሌሎች የፓርላማ አባላት ጋር በተረጋጋ መንፈስ ሲነጋገሩ ተስተውለዋል። 

ዶ/ር ጫላ በፓርላማ ቅጥር ግቢ ውስጥ በነበሩበት ወቅት፤ ሲቪል የለበሱ የፖሊስ አባላት የእርሳቸውን መውጣት ከመንገድ ዳር ሆነው ሲጠባበቁ ነበር። ሆኖም የፓርላማ አባሉ ለተጨማሪ ውይይት በቀረበላቸው ጥሪ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ በመመለሳቸው፤ የፖሊስ አባላቱ ስፍራውን ለቅቀው ሄደዋል።

አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ከፈጀው ውይይት በኋላ፤ ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ጫላ፤ “ምንም ባልል እመርጣለሁ፤ ይቅርብኝ። ሀገሬን ለ25 ዓመት አገልግያለሁ። let it be” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ዶ/ር ጫላ ይህን ምላሽ ሲሰጡም ሆነ ከሌሎች የፓርላማ አባላት ጋር ሲያወሩ ፊታቸው ላይ ፈገግታ ይታይባቸው ነበር። 

ዶ/ር ጫላ የፓርላማ አባልም ሆነ የዩኒቨርሲቲ አመራር ከመሆናቸው በፊት፤ ለረጅም ጊዜ የሰሩት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ነበር። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመምህርነት ያገለገሉት ዶ/ር ጫላ፤ ከመጀመሪያ እስከ ዶክትሬት ድረስ ያሉ ዲግሪዎቻቸውን ያገኙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ዶ/ር ጫላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በትምህርት ዕቅድ እና አስተዳደር ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በትምህርት ፖሊሲ እና ዕቅድ ሰርተዋል። የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከያዙ ሰባት ዓመታት በኋላ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ“international comparative education” የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]