የክልል ልዩ ኃይሎች አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” የሚያደርግ “ተግባራዊ እንቅስቃሴ” መጀመሩን መንግስት ገለጸ

የክልል መንግስታት ያቋቋሟቸው የልዩ ኃይሎች አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” የሚያደርግ “ተግባራዊ እንቅስቃሴ” መጀመሩን የፌደራል መንግስት አስታወቀ። የክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደ ፍላጎታቸው ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም የክልል ፖሊስ አባልነት መካተት እንደሚችሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

በሁሉም ክልሎች አመራሮች ጥናት የተደረገበት የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች የማስገባት ውሳኔ “ያለምንም ልዩነት” ስምምነት ላይ የተደረሰበት እንደሆነ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 28፤ 2015 ባወጣው መግለጫ አትቷል፡፡ እርምጃው “የኢኮኖሚ አቅማችንን በማሰባሰብ የሠራዊታችንን የሥልጠና፣ የትጥቅ እና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው” ያለው የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ፤ ይህንኑ በመረዳትም “በሁሉም ክልሎች ሂደቱ በመግባባትና በውይይት እየተከናወነ” እንደሚገኝ ገልጿል።

ይሁንና በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ “ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት” መታየታቸውን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው ኩነት  “በአንድ በኩል የመልሶ ማደራጀት ስራውን እና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሀሰት ወሬ በመጠለፍ” የተከሰተ እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል።

መንግስት በስም ባይጠቅሳቸውም “ሂደቱን ለማደናቀፍ” ይፈልጋሉ ያላቸው ኃይሎች “የመልሶ ማደራጀቱ መርኃ ግብር በአማራ ክልል ብቻ እየተካሄደ ነው፤ ህወሓት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል” የሚሉ “የሀሰት አጀንዳዎች” እያናፈሱ እንደሆነ ገልጿል።

ባለፉት 16 ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ ጸጥታ እና ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና የተጫወቱትን የክልሎች ልዩ ኃይሎች አባላት “ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ፕሮግራም” በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አስታውቋል፡፡ መግለጫው እንደሚለው፤ ይህ ሂደት የፌደራል መንግስት “በጥናት፣ በዕቅድ እና በጥንቃቄ” እየመራው የሚገኝ ነው።

የልዩ ኃይል አባላት ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች በሚገቡበት ወቅት የክልሎቹን ሰላም እና ጸጥታ ለማረጋገጥ መከላከያ ሰራዊት በሁሉም ቦታዎች ስምሪት እንደወሰደ የገለጸው መንግስት፤ በህወሓት በኩል ተነስቷል ላለው ስጋት በመግለጫው ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ፤ “ህወሓት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ” ነው ብሏል። “የህወሓት ትጥቅ የመፍታት ሂደት በተፈረመው ስምምነት መሰረት ያለማወላወል የሚፈጸም እንጂ፤ ከሌላ ሀገራዊ ዕቅድ ጋር የሚቀናጅም፣ የሚጣረስም አይደለም” ያለው መንግስት፤ “የሂደቱ ዋና ዓላማ የትኛውንም ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት” እንዳልሆነ አስታውቋል። 

በክልል መንግስታት ስር የሚገኘውን የልዩ ኃይል አወቃቀር የሚያፈርሰውን ይህን ውሳኔ ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አጥብቆ ኮንኗል። ፓርቲው በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የልዩ ኃይሉን አባላት ትጥቅ ለማስፈታት ሲሞከር “በክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌዴራል የጸጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን” ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል “ያለ በቂ ዝግጅት፣ ውይይት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይደረስ በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ኃላፊነት የጎደለው ነው” ሲል ተችቷል። የእርምጃው ዳፋ “ክልሉን እና ሃገራችን ኢትዮጵያን ወደ ሌላ የቀውስ አዙሪት የሚከት አደገኛ አካሄድ” ያለው አብን፤ “የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ” ጥሪ አቅርቧል።

በጉዳዩ ላይ ከአማራ ክልል መንግስት እና ሕዝብ ጋር “ውይይት እና ምክክር እንዲደረግ” ያሳሰበው ፓርቲው፤ የክልሉን እና የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ “ውሳኔው እንዲከለስ” ጠይቋል፡፡ አብን “የልዩ ኃይሉ ቀጣይ እጣ ፈንታ ከልዩ ኃይሉ  አመራሮች ፣ ከመላው የሠራዊቱ አባላት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በሚደረግ ውይይት እና የጋራ መግባባት ብቻ ውሳኔ ላይ እንዲደረስበት” በተጨማሪነት አሳስቧል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት “የተፈጠረው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ እና አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳይከፈል በተለመደው ጥብቅ ዲስፕሊን ፣ ጥንቃቄ  እና መረጋጋት” ራሳቸውን እንዲጠብቁ፤ “የተፈጠረው ችግር በውይይት እና በመነጋገር እንዲፈታ ጥረት” እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]