⚫ አምስቱ አሽከርካሪዎች ከቆይታ በኋላ ተለቀቅዋል ተብሏል
በአማኑኤል ይልቃል
በኦሮሚያ ክልል ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ከአዋሽ ወደ ወለንጪቲ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ 15 አሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን እና አምስቱ በተስኋላ መለቀቃቸውን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን አስታወቀ። የቀሩትን አሽከርካሪዎች ለማስለቀቅ የጸጥታ አካላት “ኦፕሬሽን” መጀመራቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገልጿል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፤ አሽከርካሪዎቹ ባልታወቁ ታጣቂዎች የታገቱት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ወለንጪቲ ከተማ አቅራቢያ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ117 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወለንጪቲ ከተማ አቅራቢያ የታገቱት አሽከርካሪዎች፤ ማዳበሪያ እና ስኳር እያጓጓዙ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ብርሃኔ፤ “የተወሰነው” ጭነት በታጣቂዎቹ መዘረፉን ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ አሽከርካሪዎቹን ወዳልታወቀ ቦታ መውሰዳቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ተሽከርካሪዎቹ ከእገታው በኋላም በቦታው ቆመው መቆየታቸውን አስረድተዋል። በአሽከርካሪዎቹ ላይ እገታ መፈጸሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር አስተባባሪ አቶ አብዱራሂም መሀመድ፤ ተሽከርካሪዎቹ ዛሬ ከእገታው ቦታ መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
የተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶች የባለቤትነት ማረጋገጫቸውን በማሳየት ከቦታው እንዲነሱ ማድረጋቸውንም አክለዋል፡፡ አቶ ብርሃኔ በበኩላቸው ከትላንት በስቲያ ከታገቱት ውስጥ አምስቱ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው ገዳ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ማህበር አሽከርካሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ አሽርካሪዎች ከቆይታ በኋላ መለቀቃቸውን፤ ይሁንና በምን አይነት መንገድ እንደተለቀቁ እስከአሁን መረጃ እንዳላገኙ አክለዋል።
የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን የታገቱትን አሽከርካሪዎች ጉዳይ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በማሳወቅ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥያቄ ማቅረቡን አቶ ብርሃኔ ጨምረው ገልጸዋል። የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ደንጌ ቦሩ፤ የአሽከርካሪዎቹ ጉዳይ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መድረሱን እና ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር ንግግር እየተደረገበት እንደሚገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው ምን ያህል ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች እንደታገቱ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ከትላንት በስቲያ በአሽከርካሪዎቹ ላይ የተፈጸመው እገታ “የጸጥታ ችግር ሲኖር የሚከሰት” መሆኑን የገለጹት አቶ ደንጌ፤ “ከዚህ በፊትም እንደዚህ አይነት ችግሮች ነበሩ” ሲሉ ይህ አይነቱ ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
የአሽከርካሪዎች እገታ የተፈጸመበት የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ማንነታቸው ያልታቀወቁ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙበት ቆይተዋል፡፡ በተለይም በዚህ ዞን ውስጥ በምትገኘው መተሐራ ከተማ እና አከባቢው፤ ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የነዋሪዎች መገደላቸው አይዘነጋም፡፡ በወለንጭቲ አቅራቢያ የታገቱትን አሽከርካሪዎችን በተመለከተ የጸጥታ አካላት አካላት በአካባቢው “ኦፕሬሽን” መጀመራቸውን የተናገሩት የትራንስፖርት እና ሎጂቲክስ ሚኒስትር ዲኤታ “መንግስት [ጉዳዩን] እየተከታተለ ነው” ብለዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)