በአማኑኤል ይልቃል
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት ኤክስፖርት ለማድረግ ካቀደችው የስንዴ ምርት ውስጥ፤ ከደቡብ ክልል የተሰበሰበው በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ላሉ ዜጎች እንዲቀርብ ሊደረግ ነው። ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል የሚከፋፈለው የስንዴ ምርት መጠን 26 ሺህ ኩንታል እንደሆነ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት የበጋ መስኖን በመጠቀም እና በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከተመረተው የስንዴ ምርት ውስጥ፤ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ተሟልቶ የሚተርፈው መጠን 32 ሚሊዮን ኩንታል ያህል እንደሆነ የፌደራል መንግስት ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ገልጾ ነበር። የፌደራል መንግስት “ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ይተርፋል” ካለው የስንዴ ምርት ውስጥ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነውን ሱዳን እና ኬንያን ጨምሮ ወደ ስድስት ሀገራት ለመላክ ውል መፈጸሙን በወቅቱ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት የምትልከው ስንዴ የሚሰበሰበው፤ ከኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራ እና ሱማሌ ክልሎች መሆኑን የስንዴ ኤክስፖርት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደበት ወቅት ይፋ ተደርጓል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው የስንዴ ኤክስፖርት ከደቡብ ክልል እንዲቀርብ የሚጠበቀው አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደሆነ ከክልሉ የግብርና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የደቡብ ክልል በዘንድሮው ዓመት ይህን ያህል የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ ቢያቅድም፤ እስካሁን ድረስ የሰበሰበው ግን 28 ሺህ ኩንታል ስንዴ ብቻ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ክልሉ ዕቅዱን ማሳካት ያልቻለው፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ስንዴ መሰብሰብ ሲጀምር በገበያ ላይ ጭማሪ በመታየቱ መሆኑን አስረድተዋል።
“እኛ ስንገባ ጠዋት 3,700 እና 3,800 የነበረ ስንዴ፤ 4,400፣ 4,500 የገባበት ሁኔታ ነው ያለው። ለኤክስፖርት ስንዴ ይሰበሰባል የሚል ያልተገባ መረጃ በመርጨት በዚህ የሚያተርፉ አሉ” ሲሉ የክልሉ መንግስት በዚህ ረገድ ያጋጠመውን ተግዳሮት አብራርተዋል። በዚህም ምክንያት የክልሉ መንግስት “የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ በሚል” ስንዴ የመሰብሰብ ስራውን ለጊዜው እንዲቆይ ማድረጉን አስረድተዋል።
የደቡብ ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አምሪያ ሲራጅ በበኩላቸው፤ ክልሉ ኤክስፖርት ለማድረግ ከአርሶ አደሮች ከሰበሰበው ስንዴ ውስጥ 26 ሺህ ኩንታል ያህሉን በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማቅረብ መወሰኑን አስታውቀዋል። “ስንዴው የታሰበው ለኤክስፖርት ነበር። ነገር ግን አሁን ሀገር ውስጥም ረጅም ጊዜ ዝናብ ካለመዝነቡ ጋር በተያያዘ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እየጨመረ ነው። ስለዚህ ሃሳቡ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ለማከፋፈል፣ ለማድረስ ነው” ሲሉ ውሳኔውን አብራርተዋል።

የስንዴ ምርቱን ከደቡብ ክልል ገዝቶ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የማከፋፈል ስራን የሚያከናወነው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እንደሚሆንም ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ መጋቢት 27፤ 2015፤ በክልሉ ከሚገኙ ህብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር ውል መፈራረሙን አስታውቀዋል። ይህ ስምምነት በኮሚሽኑ በደቡብ ክልል መካከል የተፈረመው፤ ድርቅ ለተከሰተባቸው አካባቢዎች “ቅድሚያ እንዲሰጥ” በፌደራል መንግስት በተላለፈ ውሳኔ መሰረት መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ይህን የስንዴ ምርት የሚያከፋፍለው፤ በደቡብ እና በሌሎችም ክልሎች “እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በተለዩ” አካባቢዎች እንደሆነ አቶ ኡስማን አመልክተዋል። በደቡብ ክልል በኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም በቡርጂ፣ ደራሼ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ በርካታ ነዋሪዎች የምግብ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።
ከደቡብ ክልል ስንዴ ለመግዛት ስለተፈጸመው ውል ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አይደሩስ ሀሰን፤ የፊርማ ስምምነት መደረጉን አረጋግጠዋል። “ከእነሱ ጋር ውል አድርገናል። በውሉ መሰረት ይቀርባል፣ አይቀርብም ገና ምናውቀው ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የደቡብ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ግን ኮሚሽኑ ውል የገባበት 26 ሺህ ኩንታል ስንዴ፤ ለኤክስፖርት ተብሎ ከተሰበሰበው 28 ሺህ ኩንታል ምርት ውስጥ የሚሰጥ በመሆኑ የአቅርቦት ችግር እንደማያሳስብ ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN OCHA) በመጋቢት ወር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በደቡብ፣ ሶማሌ እና ኦሮሚያ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ብዛት 24 ሚሊዮን ነው። ከእነዚህ ነዋሪዎች ውስጥ የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል ተብለው የሚገመቱት 11 ሚሊዮን ያህሉ እንደሆኑ የቢሮው መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)