የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች፤ በየካምፖቻቸው ወይም በተመደቡበት የስራ ቦታ በመመለስ ተረጋግተው እንዲጠብቁ ጥሪ ተላለፈ

በአማኑኤል ይልቃል

የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች በየካምፖቻቸው ወይም በተመደቡበት የስራ ቦታ በመመለስ ተረጋግተው እንዲጠብቁ የክልሉ መንግስት ጥሪ አስተላለፈ። የአማራ ክልል መንግስት፤ የክልሉን ህዝብ “መብት እና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም አይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግም” አስታውቋል።

የአማራ ክልል ይህን የገለጸው፤ የልዩ ኃይሎች መልሶ የማደራጀት ስራን አስመልክቶ ዛሬ አርብ መጋቢት 29፤ 2015 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው፤ የልዩ ኃይል ፖሊስን መልሶ የማደራጀት ተግባር፤ “በሁሉም ክልሎች ታምኖበት የተገባበት ወሳኝ ተግባር ነው” ብሏል።  

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘው ይህ የሪፎርም ተግባር፤ የፌዴራል እና የክልል የጸጥታ አካላትን የማጠናከር ዓላማ ያነገበ ቢሆንም፤ በአንዳንድ አካላት ግን “የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው” የሚል “ሀሰተኛ መረጃ” እየተሰራጨ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል። የክልሉ መንግስት “ሀሰተኛ መረጃ” ያሰራጫሉ ያላቸው በስም ያልጠቀሱ አካላት፤ “የአማራ ህዝብ ውስጣዊ ሰላም እና አንድነት የሚያደፈርስ፣ የልዩ ኃይሉን አንድነት የሚረብሽ፣ ባልተገባ መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ” የሚያደርግ እንቅስቃሴ ላይ መሰማራታቸውን ገልጿል።

“ድርጊቱ ህዝባችንና የልዩ ኃይል አባሎቻችንን በተጨባጭ እየረበሸ ይገኛል” ሲል በሚሰራጨው መረጃ ምክንያት ችግር ማጋጠሙንም የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው አስታውቋል። የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ ለማደራጀት በተጀመረው ስራ ምክንያት “ምንም አይነት የሚበተን ኃይል እንደሌለ” የልዩ ኃይል አባላት እና የክልሉ ህዝብ እንዲገዘነቡለትም ክልሉ በዛሬው መግለጫው ጠይቋል።

መልሶ የማደራጀቱ ስራ “የልዩ ኃይላችንን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀትና ብቁ የማድረግ አገራዊና ክልላዊ ፋይዳ የማዘጋጀት ተግባር [ነው]” ሲልም የክልሉ መንግስት አጽንኦት ሰጥቷል። የክልሉ ህዝብ “በሚነዛ አሉባልታ እንዳይታለል እና እንዳይደናገር” የጠየቀው የዛሬው መግለጫ፤  “የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ሕዝብ መብት እና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም አይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ” ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል” ብሏል።

የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ ለማደራጀት የተጀመረው ስራ፤ የክልሉን ህዝብ እና የልዩ ኃይል አባላትን “በማወያየት እና በመተማመን የሚፈጸም” መሆኑን የክልሉ መንግስት በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። በመሆኑም የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት፤ በየካምፖቻቸው ወይም በየተመደቡበት የስራ ቦታ በመመለስ፤ መልሶ የማደራጀት ስራውን “ተረጋግተው በትግስት እንዲጠብቁ” የክልሉ መንግስት ጥሪውን አስተላልፏል። የልዩ ኃይል አባላቱ፤ የክልሉን “የጸጥታ ኃይል ብቁ ዘብ በመሆን” ሰላም እና ጸጥታን በማስጠበቅ ስራ ላይ እንዲተጉም በመግለጫው አሳስቧል።

የአማራ ክልል መንግስት የዛሬውን ጥሪ እና ማሳሰቢያ ያቀረበው፤ የፌደራል መንግስት የልዩ ኃይል አባላትን “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” የማድረግ ስራውን “የሚያውኩ ተግባራት” በክልሉ እንዳጋጠመው ባስታወቀ ማግስት ነው። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ትላንት ባወጣው መግለጫ ሂደቱ በአማራ ክልል ችግር ያጋጠመው፤ “በተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች” ውስጥ እንደሆነ ገልጾ ነበር።

የፌደራል መንግስት በክልሉ አጋጥሞኛል ላለው ችግር ሁለት ምክንያቶችን የጠቀሰ ሲሆን፤ በቀዳሚነት ያስቀመጠው “የመልሶ ማደራጀት ስራውንና ዓላማውን በአግባቡ አለመረዳት” የሚል ነው። የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት “የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሀሰት ወሬ መጠለፍንም” በምክንያትነት አንስቷል። በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ይህ እርምጃ የተጀመረው፤ “የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሰራዊት ለመገንባት” በመወሰኑ መሆኑን በመግለጫው አስረድቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሏል]