የአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ያደረጉት ውይይት “አዎንታዊ እርምጃ የታየበት ነው” አሉ  

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ባለሙያዎች፤ ለኢትዮጵያ “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” ሁለተኛ ምዕራፍ ስለሚደረገው ድጋፍ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ያደረጉት ውይይት አዎንታዊ እርምጃ ማሳየቱን አስታወቁ። ውይይቱ በሚቀጥለው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ በሚካሄደው የድርጅቱ እና የዓለም ባንክ ስብሰባ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። 

የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ይህን የገለጹት፤ ከመጋቢት 18 ጀምሮ እስከ ዛሬ አርብ መጋቢት 29፤ 2015 በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ነው። ለሁለት ሳምንት ገደማ በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረገው የባለሙያዎች ቡድን መሪ የሆኑት አልቫሮ ፒሪስ ዛሬ በተቋሙ በኩል ባወጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ይፋ አድርገዋለሁ ስላለው ሁለተኛ ምዕራፍ “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” አንስተዋል። 

የኢኮኖሚ ማሻሻያውን “ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ድክመቶችን ለመፍታት እና የኢትዮጵያን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማስፋት ያለመ” ሲሉ የገለጹት ፒሪስ፤ አይ ኤም ኤፍ ለዚህ የማሻሻያ ፕሮግራም በሚያደርገው የድጋፍ መጠን ላይ የድርጅቱ ባለሙያዎች ከመንግስት ባለስልጣናት ያደረጉት ውይይት “አዎንታዊ እርምጃ አሳይቷል” ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባለፈው ሳምንት ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር “ጥሩ ውይይት” መጀመሩን ተናግረው ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት “ለማቃለል የሚያስችሉ ድጋፎች” ከአይ ኤም ኤፍ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ገልጸዋል። 

የአይ ኤም ኤፍ የድጋፍ ፕሮግራም፤ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ድርድር ለማጠናቀቅ የሚያስፈልግ ቅድመ ሁኔታ ጭምር ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ገብተዋል ከሚላቸው አገራት ጎራ የምትመደበው ኢትዮጵያ፤ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የአከፋፈል ማሻሻያ እንዲደረግላቸው በቅድሚያ ጥያቄ ካቀረቡ ሶስት አገራት አንዷ ናት።

ኢትዮጵያ መክፈል በሚጠበቅባት ዕዳ ላይ ሽግሽግ ለማድረግ የተጀመረው ድርድር እጅግ ቢዘገይም፤ መንግስት ከቻይና፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ ያደረጋቸው ውይይቶች “አዎንታዊ” መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ በባለፈው ሳምንት ቃለ ምልልሳቸው ጠቅሰው ነበር። “በኮመን ፍሬም ወርኩ በኩል የሚደረጉ ውይይቶች፤ ቻይናም ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አሳውቃለች። ከፈረንሳይ ጋር የነበረው ውይይትም በጣም ጥሩ ነበር” ሲሉ አቶ አህመድ ሂደቱ ያለበትን ደረጃ አስረድተዋል።

ይኸው የዕዳ ሽግሸግ ጉዳይ፤ በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት ላይም ተነስቶ ነበር። በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የኢትዮጵያን ዕዳ ለማሸጋሸግ የተጀመረውን ሂደት የአሜሪካ መንግስትም “በጠንካራ ሁኔታ እንደሚደግፍ” ብሊንከን ማሳወቃቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)