በሃሚድ አወል
በፌደራል መንግስት ወደ ፊት የሚቋቋሙ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች፤ ራስ ገዝ ሆነው እንደሚደራጁ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ተናገሩ። ወደ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገቡ ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት፤ ከፍለው የሚማሩ መሆን እንዳለባቸውም ሚኒስቴር ዴኤታው አስታውቀዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ይህን ያሉት፤ ስለ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመደንግግ በወጣው የአዋጅ ረቂቅ ላይ በተጠራ የአስረጂ መድረክ ላይ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 2፤ 2015 የተደረገውን ይህን የአስረጂ መድረክ የጠራው፤ የፓርላማው የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው።
በስድስት ክፍሎች እና 45 አንቀጾች የተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቅ፤ በመጀመሪያ ለፓርላማ የቀረበው መጋቢት 21፤ 2015 ነበር። አዋጁ የቀረበላቸው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲመለከተው በሙሉ ድምጽ መርተውት ነበር። ይህን ተከትሎ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው በዛሬው የአስረጂ መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር ሳሙኤል በዚሁ መድረክ ላይ ባቀረቡት ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የሚሆኑበትን ሂደት አብራርተዋል። “አዋጁ ባስቀመጠው መልኩ ዩኒቨርሲቲዎች መስፈርት ሲያሟሉ፤ ደንቦቻቸው በዚህ አዋጅ መሰረት መልሶ እንዲከለስ ይደረግ እና ራስ ገዝ ሆነው መልሰው ይደራጃሉ” ብለዋል። ለፓርላማው የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ፤ “ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እና አካዳሚያዊ ተወዳዳሪነት” ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ከሚያበቁ መስፈርቶች መካከል እንደሚካተቱ አስፍሯል።
ይህ አዋጅ በፓርላማ ከጸደቀ በኋላ “ራስ ገዝ” የሚሆኑት፤ አሁን በትምህርት ሚኒስቴር ስር የሚተዳደሩ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ አለመሆናቸውን ዶ/ር ሳሙኤል በዛሬው ማብራሪያቸው ጠቁመዋል። “መስፈርቱን አሟልተው የሚፈጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲኖሩ፣ ወደፊት አዲስም ቢሆኑ፤ እንደራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ይደራጃሉ” ሲሉ አዋጁ ወደፊት የሚቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎችንም የሚመለከት መሆኑን ሚኒስቴር ዴኤታው አስረድተዋል።
ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማቋቋም የተዘጋጀው አዲሱ አዋጅም፤ ይህንኑ ጉዳይ የተመለከተ ድንጋጌ አካትቷል። ስለ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች መቋቋም የሚደነግገው የአዋጁ ክፍል፤ “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ይቋቋማል” ይላል። በዚህ መልኩ የሚመሰረተው ዩኒቨርሲቲ፤ “በከፍተኛ ትምህርት አዋጁ መሰረት የተቋቋመ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ወይም አዲስ ዩኒቨርሲቲ ሊሆን ይችላል” ሲልም የአዋጅ ረቂቁ ያትታል። አሁን በስራ ላይ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ዕውቅና የሚሰጠው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ የጸደቀው፤ ከሶስት ዓመት ከመንፈቅ በፊት በ2011 ዓ.ም ነበር።
በዛሬው የአስረጂ መድረክ በመንግስት ወደፊት ስለሚቋቁሙ ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳይ ቢነሳም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግን መንግስታቸው በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ውስጥ “አንድም ዩኒቨርሲቲ” የመክፈት ዕቅድ እንደሌለው አስታውቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ህዳር ወር በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ በሚቀጥሉት አራት አመታት የመንግስታቸው ትኩረት ከመዋለ ህጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት “አስተማማኝ መሰረት መጣል” መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው “ዩኒቨርሲቲዎች በደንብ ጠንክረው ራስ ገዝ እየሆኑ ሲሄዱ፤ እኛ አዲስ እያስፋፋፈን መሄድ አንቸገርም” ሲሉ አዲስ ዩኒቨርሲቲ ከመክፈቱ በፊት ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው በስራ ላይ ያሉትን አደረጃጀት መቀየር መሆኑን አመልክተው ነበር። ይህ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የማድረጉ ሂደት፤ በተያዘው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሮ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ዶ/ር ሳሙኤል ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታውን ገለጻ ተከትሎ፤ ከተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥያቄዎች ተነስተዋል። የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ክፍያ በተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ፍሬው ተስፋዬ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፤ “የሚጣሉ ክፍያዎችን በተመለከተ የዜጎችን አቅም ያገናዘበ ለማድረግ እና ዜጎች የመማር ዕድል እንዳያጡ ለማስቻል ምን ታስቧል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪ አይመደብላቸውም” ብለዋል። ሆኖም ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን በተመለከተ “የፍትሃዊነት ማምጫ መንገዶችን” ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። በዶ/ር ሳሙኤል ከተጠቀሱት “የፍትሃዊነት ማምጫ መንገዶች” ውስጥ፤ “ለተማሪዎች ሙሉ እና ከፊል ነጻ የትምህርት ዕድል መስጠት” የሚለው ይገኝበታል።
መንግስት ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያደርገውን የበጀት ድጋፍ እና ቀመር ለመወሰን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣው ደንብ፤ በሚኒስትር ዴኤታው የተጠቀሰው ሌላኛው “ፍትሃዊነትን ማምጫ” መንገድ ነው። “ደንቡ ፍትሃዊነትን የሚያስተናግድበት ክፍል አለው” ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል፤ “ማስገደጃ እና ማትጊያ” ድንጋጌዎችን አካትቶ እንደሚጸድቅ ጠቁመዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው መስሪያ ቤታቸው የፍትሃዊነት ጥያቄን ለመመለስ የሚከተላቸውን መንገዶች ቢያብራሩም፤ በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች አብዛኞቹ ተማሪዎች ክፍያቸውን ራሳቸው የሚሸፍኑ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል። በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች “ከግማሽ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ከፍለው የሚማሩ ሊሆን ይገባል” ሲሉም ተደምጠዋል። በዚህም ምክንያት በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሴኔት አባላት አወቃቀር፤ የተማሪዎች ድምጽ ከፍ ያለ እንዲሆን መደረጉን አንስተዋል።
በዛሬው መድረክ ተሳታፊዎች ተደጋግሞ የተነሳው ሌላኛው ጥያቄ፤ ከራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የንግድ ድርጅት ማቋቋም ጋር የተገናኘ ነው። “ዩኒቨርሲቲዎች በንግድ ስራ መሰማራታቸው የትምህርት ጥራት ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም ወይ?” የሚል ጥያቄ ከቋሚ ኮሚቴው ቀርቧል። ረቂቁ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፓርላማ በቀረበበት ወቅትም ተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። አቶ አዳነ ማንዴ የተባሉ የፓርላማ አባል በዚሁ ስብሰባ ወቅት፤ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎቹ “የትምህርት ጥራቱን፣ ሌሎች ነገሮችን ትተው ገንዘብ ማግኘት ላይ ብቻ ሊያተኩሩ ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።
ዶ/ር ሳሙኤል ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኳቸው ውጤታማ ለመሆን ሀብት ያስፈልጋቸዋል። ያ ሀብት በተፈቀደ መልኩ በህግ አግባብ የሚያመነጩት፤ ስራ ላይ የሚያውሉት መሆን አለበት። ለዚያ ስርዓት መዘርጋት አለበት” ብለዋል። ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎቹ “የንግድ ድርጅትም ቢያቋቁሙ፤ ሌላ ነጋዴ መስራት የሚችለውን ሳይሆን ከተልዕኳቸው ጋር የሚመጋገብ” መሆን እንዳለበት ያስረዱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በዚህ ረገድ የሚኖራቸው ፍቃድ “ምግብ ለመሸጥ ወይም ቡቲክ ለመክፈት” የሚውል እንዳልሆነ አብራራተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)