በደብረ ብርሃን ከተማ ከጸጥታ ኃይሎች ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከለከለ

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት፤ ለጸጥታ ማስከበር ተልዕኮ ከተሠጠው የጸጥታ ኃይል ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን ከለከለ። በከተማይቱ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ተፈናቃዮች፤ “ወቅታዊ ሁኔታው እስኪስተካከል ድረስ” ከካምፕ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱም አግዷል።

ኮማንድ ፖስቱ ክልከላዎቹን ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 2፤ 2015 ያስተላለፈው፤ “የከተማዉን ሰላም እና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እንዲቻል” በሚል ነው። በዛሬው ዕለት ከተላለፉት 14 ክልከላዎች ውስጥ፤ ያለ መንግስት እውቅና ስብሰባዎችን እና ሰልፎችን ማድረግ ያገደው ይገኝበታል። በኮማንድ ፖስቱ ውሳኔ መሰረት፤ መንገድ መዝጋት፣ አድማ መቀስቀስ፣ ማድረግ እና ማስተባበር እንዲሁም መደበኛ ስራን ማስተጓጎል በጥብቅ ተከልክሏል።

ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው በደብረ ብርሃን ከተማ፤ “ህጋዊ መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ በጥብቅ መከልከሉንም” ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል። ህጋዊ መታወቂያ ሳይዝ የተንቀሳቀሰ ግለሰብም ሆነ ቡድን በህግ ቁጥጥር ስር እንደሚውልም የከተማይቱ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት አስጠንቅቋል።

ዛሬ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት፤ በደብረ ብርሃን ከተማ “በማንኛውም ቦታ እና ሰዓት ጥይትም ሆነ ርችት መተኮስ” ተከልክሏል። ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ በተላለፈው ውሳኔ ላይ “በተፈጠረ የመረጃ ክፍተት ከተለያዩ አካባቢዎች ተነስተው ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ የገቡ” የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት እንዳሉ የገለጸው ኮማንድ ፖስቱ፤ የጥይት መተኮስ ክልከላውን እነርሱንም ጭምር እንደሚመለከት አስታውቋል። 

እነዚሁ የልዩ ኃይል አባላት በተናጠልም ሆነ በቡድን መሳሪያ ይዘው መንቀሳቀስም ተከልክለዋል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ የክልሉን ፓሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስን፤ ከጸጥታ ኃይሎች አባላት ውጭ መልበስ እንደማይቻልም በዛሬው መግለጫ ላይ ሰፍሯል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ኮማንድ ፖስት ያስተላለፋቸው አብዛኞቹ ክልከላዎች፤ በዛሬው ዕለት ቀድሞ ይፋ ከተደረጉት የጎንደር እና የደሴ ከተማ ውሳኔዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ሶስቱም ከተማዎች በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡባቸውን ጊዜያቶች ገድበዋል። እነዚህ ተሽከርካሪዎች በደብረ ብርሃን እና ጎንደር ከተሞች ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ተከልክለዋል። የደሴ ከተማ በባጃጆች ላይ የጣለው ገደብ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል የሚጀምር ነው።

ሶስቱም ከተሞች ባስተላለፏቸው የክልከላ ዝርዝሮች ውስጥ፤ “በህግ የሚፈለጉ ወይም ተጠርጣሪዎችን ሽፋን መስጠት፣ መደበቅ ፣ የሀሰተኛ መረጃ ሰጥቶ ማስመለጥ” በህግ የተከለከለ መሆኑን አስፍረዋል። የጸጥታ ኃይሎችን የህግ ማስከበር ተልዕኮ “ማደናቀፍ እና ማወክም” እንደማይቻል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። በእነዚህ ከተሞች “ጸጉረ ልውጥ ወይም አጠራጣሪ ሰው”፤ ከቤቱ ያሳደረ፣ ያከራየ፣ በሆቴሉ አልጋ ያስያዘ እንዲሁም ለሚመለከተዉ የጸጥታ አካል ጥቆማ ያልሰጠ ግለሰብም በህግ እንደሚጠየቅ በመግለጫዎቹ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)