በሃሚድ አወል
ከትላንት በስቲያ እሁድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋ መስከረም አበራ፤ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ተጠርጥራ በፍርድ ቤት 13 የምርመራ ቀናት ተፈቀደባት። መስከረምን ፍርድ ቤት ያቀረባት የፌደራል ፖሊስ፤ “ተጠርጣሪዋ ለኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወታደራዊ ስልጠና እና የተኩስ ልምምድ ስትሰጥ ነበር” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ፖሊስ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዚያ 3፤ 2015፤ በመስከረም ላይ ውንጀላውን ያቀረበው፤ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። በችሎቱ መስከረምን ወክለው የቀረቡት ጠበቃዋ አቶ ሄኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።
መስከረምን ከትላንት በስቲያ ምሽት በቁጥጥር ስር ያዋሏት የጸጥታ ኃይሎች “የፈለጋት የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው” ማለታቸውን ባለቤታቸው አቶ ፍጹም ገብረ ሚካኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸው የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት ጉዳይዋ የተያዘው በፌደራል ፖሊስ መሆኑ ታይቷል። የፌደራል ፖሊስን ወክለው በችሎት የተገኙት መርማሪ፤ መስከረም የተጠረጠረችበትን ጉዳይ በንባብ ለችሎቱ አስረድተዋል። መርማሪው ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በየመሃሉ በቃላቸው ሲያክሉ ተስተውለዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋ “የፖለቲካ ዓላማዋን ለማሳካት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም፤ ህገ ወጥ ቡድን በማደራጀት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መረጋጋት እንዳይኖር እና ግጭት እንዲቀሰቀስ ስትሰራ ነበር” ሲል የፌደራል ፖሊስ ውንጀላውን ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል። መስከረም “ወጣቶችን ስታደራጅ ነበር” ያለው የፌደራል ፖሊስ፤ “በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭት እና ሁከት ለመቀስቀስ ስትንቀሳቀስ ነበር” ሲል የተጠረጠረችበትን ወንጀል ዝርዝር አብራርቷል።
ፖሊስ አክሎም “የተደራጁትን ወጣቶች እና ኢ- መደበኛ አደረጃጀቶችን ለአመጽ ተግባር ወታደራዊ ስልጠና እና የተኩስ ልምምድ ጭምር ስትሰጥ ነበር” ሲል መስከረምን የጠረጠረበትን ተጨማሪ ወንጀል ለችሎቱ ገልጿል። በተጠርጣሪዋ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው ምርመራ “ጅምር መሆኑን” ለፍርድ ቤት የገለጸው የፌደራል ፖሊስ፤ የሰው እና ሰነድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ፍርድ ቤቱ 14 የምርመራ ቀናትን እንዲፈቅድለት ጠይቋል።
ፖሊስ የጠቀሳቸው ወንጀሎች “መቼ ተፈጸሙ የሚለውን ፍሬ ነገር አላቀረበም” ያሉት የመስከረም ጠበቃ አቶ ሄኖክ በበኩላቸው፤ ደንበኛቸው የተያዙት “በዘመቻ እስር” እንጂ “የወንጀል ባህሪ ያለው ነገር ፈጽመው አለመሆኑን” ጠቅሰው ተከራክረዋል። አቶ ሄኖክ አክለውም፤ “በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ተፈጸመ በተባለው ወንጀል ስለደረሰ ጉዳት የተገለጸ ነገር የለም” ብለዋል። “ደንበኛቸው የታሰሩት በአማራ ህዝብ ላይ ለሚፈጸም ግፍ፤ የአማራ ህዝብ ጠበቃ በመሆናቸው ነው” ያሉት ጠበቃ ሄኖክ፤ “የተፈጸመ ወንጀል የለም” ሲሉ ተሟግተዋል።
የመስከረም አበራን አቆያየት በተመለከተም፤ “ፖሊስ ‘ልሰበስባቸው ይገባሉ’ ያላቸውን ማስረጃዎች ሁሉ በብርብራ ሰብስቧል” ሲሉ ፍርድ ቤቱ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል። “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ ባለፈው እሁድ በቁጥጥር ስር ስትውል፤ 50 ደቂቃ ገደማ የፈጀ “ብርበራ” በመኖሪያ ቤቷ መከናወኑን ባለቤቷ አቶ ፍጹም ገብረ ሚካኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። ከዚሁ ፍተሻ በኋላ፤ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ሶስት የመስከረም አበራ ረቂቅ ጽሁፎችን እና የእርሷን “ሳምሰንግ” ሞባይል እንደወሰዱ ባለቤቷ መግለጻቸው ይታወሳል።
በዛሬው የችሎት ውሎ የተጠርጣሪዋ ጠበቃ፤ ደንበኛቸው “በዋስትና ቢወጡ በምርመራው ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉት መሰናክል አልተጠቀሰም። አሁን ባለው ሁኔታ የደንበኛዬን ዋስትና ሊያስከለክል የሚችል ሁኔታ የለም” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል። በጠበቃ ሄኖክ በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ የተቃወመው መርማሪ ፖሊስ፤ “መስከረም ህዝብን እና ወጣቱን ወደ አመጽ፤ ሀገርን ወደ ለየለት ሁከት የሚመራ ወንጀል” መፈጸሟን በማንሳት የጠየቀው የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ ለፌደራል ፖሊስ የ13 ቀናት የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል። ችሎቱ የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው በሶስት ምክንያቶች እንደሆነ ገልጿል። የመጀመሪያው ምክንያት “መርማሪ ፖሊስ ለምርመራ መነሻ የሚሆን ማስረጃ ማቅረቡን በመረዳት” መሆኑን ያስታወቀው ችሎቱ፤ ሁለተኛው “የወንጀሉን ክብደት” ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ገልጿል። በተጠርጣሪዋ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ “ጅምር መሆኑ” ታሳቢ መደረጉንም ችሎቱ በተጨማሪ ምክንያትነት ጠቅሷል።
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ በቁጥጥር ስር የዋለችው መስከረም፤ የዛሬውን የችሎት ውሎ በአካል ተገኝታ ተከታትላለች። መስከረም አበራ ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው፤ ከአስራ አንድ ወራት ገደማ በፊት በግንቦት 2014 ዓ.ም ነበር። በራሷ እና በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን በምታቀርባቸው የፖለቲካ ትንታኔዎች ይበልጥ የምትታወቀው መስከረም ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረችው ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነው። በዚህ ወቅት የፌደራል ዐቃቤ ህግ “ጥላቻ፣ አመጽ፣ ሁከት እና ግጭት የመቀስቀስ” ክስ የመሰረተባት ሲሆን፤ በዋስትና ከእስር ተለቅቃ ጉዳይዋን በውጭ ሆና እየተከታተለች ባለችበት ለሶስተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሏል]