በአማኑኤል ይልቃል
በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት ለሶስት ቀናት ተዘግቶ የነበረው የደጀን መንገድ፤ ዛሬ ጠዋት ላይ መከፈቱን አንድ የከተማይቱ አስተዳደር ኃላፊ እና ነዋሪዎች ተናገሩ። ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፤ ከአዲስ አበባ በደጀን ከተማ በኩል ወደ ባህር ዳር ለሚደረግ ጉዞ ገና ትኬት መቁረጥ አለመጀመራቸውን ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ከተማ የሚወስደው አውራ ጎዳና፤ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በምትገኘው ደጀን ከተማ የተዘጋው፤ ባለፈው ሳምንት አርብ መጋቢት 29፤ 2015 ዓ.ም ነበር። የአማራ ክልል “ልዩ ኃይል መበተንን የሚቃወሙ” የተባሉ ነዋሪዎች፤ በከተማዋ መግቢያ እና ውስጥ ባሉ ቦታዎች መንገዱን ከዘጉ በኋላ በደጀን በኩል የሚያልፉ የህዝብ እና የጭነት ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች መተላለፍ አቁመው ቆይተዋል።
ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 3፤ 2015 ጠዋት ከሁለት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ግን፤ ለቀናት ተዘግቶ የነበረው መንገድ ተከፍቶ ቆመው የነበሩ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ እንደጀመሩ የከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ሞኙ ሆዴ አሳየ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቡድን መሪው እንደሚያስረዱት መንገዱ የተከፈተው፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ዛሬ ጠዋት ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተከትሎ ነው።
በደጀን ከተማ የተለያዩ ቦታዎች መንገድ ለመዝጋት ተቀምጠው የነበሩ ድንጋዮች፤ በመከላከያ ወታደሮች እና በአካባቢው ነዋሪዎች አማካኝነት መነሳቱን የቡድን መሪው ገልጸዋል። መንገዱ “በዶዘር” ከተጠረገ በኋላ ክፍት መደረጉንም ጠቁመዋል። መንገድ በመዝጋት መንግስት ከልዩ ኃይል አደረጃጀት ለውጥ ጋር በተያያዘ የጀመረውን ስራ የተቃወሙ ነዋሪዎች፤ ዛሬ ጠዋት የከተማዋ መንገድ ሲከፈት እና ድንጋዮች ሲነሱ ተቃውሞ አለማሰማታቸውንም አክለዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ይህንን አረጋግጠዋል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ “መከላከያው ሲገባ ምንም ተቃውሞ አልነበረም። ቀጥታ ነው የገባው። መንገድ ላይ የሚያገኛቸውን [ድንጋዩን] አንሱት እያዘዘ ነው ያስነሳው” ብለዋል። ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው “ምንም ችግር ነገር አልነበረም። መንገዱ ሲከፈት ወጣቱ በየመንገዱ ዳር ቆሞ ነበር” በማለት በዛሬው ዕለት በከተማዋ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።
ለቀናት የተዘጋው መንገድ በመከላከያ ሰራዊት አባላት አማካኝነት መከፈቱን ተከትሎ፤ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ቆሞ የነበረው የደጀን ከተማ የንግድ እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ዳግም መጀመሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በከተማዋ የሚገኙ ባንኮች ከሰዓት በኋላ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩ የኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪው አቶ ሞኙ ሆዴ አስታውቀዋል።
መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ከደጀን ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚያደርገውን የመንገደኞች ጉዞ አቁሞ የነበረው ዋልያ ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ፤ ዛሬ ከከተማዋ ወደ አዲስ አበባ አውቶብስ ማሰማራቱን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። ይሁንና ዋልያ እና አባይ ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፤ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ለሚደረግ ጉዞ የተሳፋሪዎች ትኬት መቁረጥ አለመጀመራቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)