ከአዲስ አበባ ኮንዶሚኒዬም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በ“ከባድ የሙስና ወንጀል” ከተከሰሱ ግለሰቦች ውስጥ አምስቱ በፍርድ ቤት ነጻ ተባሉ

በሃሚድ አወል

የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያና ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን ጨምሮ፤ ከኮንዶሚኒዬም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ “ከባድ የሙስና ወንጀል” ክስ የተመሰረተባቸው አምስት ግለሰቦች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነጻ ተባሉ። በዚሁ መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ግለሰቦች መካከል አንድ ተከሳሽ በሌሉበት ጥፋተኛ ሲባሉ፤ ቀሪ አምስት ተከሳሾች ደግሞ የተከሰሱበት ድንጋጌ ተቀይሮ እንዲከላከሉ በፍርድ ቤቱ በይኗል።

ይህን ብይን የሰጠው ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 4፤ 2015 የዋለው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ችሎት ነው። ችሎቱ አምስት ተከሳሾችን በነጻ ያሰናበተው፤ “ዐቃቤ ህግ ባቀረበው የሰው እና የሰነድ ማስረጃ፤ ወንጀሉን በበቂ ሁኔታ ባለማስረዳቱ” መሆኑን ገልጿል። በነጻ ከተሰናበቱት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ሙያና ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ አብርሃም ሰርሞሎ እና የከተማይቱ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቢሮ የአይሲቲ ዳይሬክቶሬይትን ሲመሩ የነበሩት አቶ ኩምሳ ቶላ ይገኙበታል።

ሶስቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ጨምሮ በአስራ አንድ ግለሰቦች ላይ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ላቀረበው ክስ ምክንያት የነበረው፤ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 1፤ 2014 በአዲስ አበባ ከተማ በወጣው የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ዕጣ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል የተባለው የማጭበርበር ወንጀል ነው። የዕጣው ማውጣት ስነ ስርዓቱ ከተከናወነ ከአምስት ቀናት በኋላ፤ ፖሊስ ስምንት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል። 

ገዢው ብልጽግና ፓርቲን በመወከል የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ሙሉቀን፤ ያለመከሰስ መብታቸው በምክር ቤቱ ተነስቶ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሐምሌ 8፤ 2014 ነበር። የፌደራል ዐቃቤ ህግ ዶ/ር ሙሉቀንን ጨምሮ በአስራ አንድ ተጠርጣሪዎች ላይ “ከባድ የሙስና ወንጀል” በመፈጸም ክስ የመሰረተባቸው፤ ከሰባት ወራት በፊት መስከረም 11፤ 2015 ነበር። 

በዶ/ር ሙሉቀን እና ከእሳቸው ስር ሆነው ሲሰሩ በነበሩት በአቶ አብርሃም ላይ ቀርቦባቸው የነበረው ክስ፤ “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል” ፈጽመዋል የሚል ነበር። ሁለቱ ተከሳሾች የኮንዶሚኒዬም ዕጣ የወጣበት ሲስተም፤ “ችግሮች እያሉበት ለዕጣ ማውጣት እንዲውል በማድረግ” ተወንጅለው ነበር። 

ሆኖም የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ሁለቱ ግለሰቦች “የፖለቲካ ተሿሚዎች ስለሆኑ ቴክኒካል እና ዝርዝር የሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፎ የላቸውም” ማለታቸው በዛሬው የችሎት ውሎ ተገልጿል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ብይንን በንባብ ያሰሙት የቀኝ ዳኛ “ዐቃቤ ህግ ባሰማው ማስረጃ ክሱን በተገቢው መንገድ ያስረዳ ባለመሆኑ፤ ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ በሙሉ ድምጽ ተወስኗል” ብለዋል። 

በዚሁ ክስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኃላፊነት ሲሰሩ የቆዩት አቶ ኩምሳ ቶላ በተመሳሳይ “ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” በሚል ተወንጅለው ነበር። አቶ ኩምሳ የተወነጀሉት “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ስራን በማያመች አኳኋን” መርተዋል በሚል ነው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቢሮ የአይሲቲ ዳይሬክቶሬይት ዳይሬክተር የነበሩትን ኃላፊ ለዚህ ክስ የዳረጋቸው፤ የኮንዶሚኒዬም ተመዝጋቢዎች “ዳታ” እንዳይቀየር ሊጠብቁት ሲገባቸው “ከፍተኛ ክፍተት እንዲፈጠር በማድረጋቸው” መሆኑን በዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ ላይ ሰፍሯል። 

ሆኖም የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎቱ፤ አቶ ኩምሳ “ዳታ እንዳይቀየር የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን” እና “የተመዝጋቢዎችን ዳታ በብቸኝነት ይዘው የነበሩ መሆናቸውን” ዐቃቤ ህግ “በበቂ ሁኔታ አላስረዳም” ብሏል። ይህን ተከትሎም አቶ ኩምሳ፤ እንደ ዶ/ር ሙሉቀን እና አቶ አብርሃም ሁሉ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በሙሉ ድምጽ ከተከሰሱበት ወንጀል ነጻ ተብለዋል። ከሶስቱ ኃላፊዎች በተጨማሪ በመዝገብ ክሱ ተራ ቁጥር ስድስት እና 11 ላይ የተጠቀሱ ተከሳሾችም እንዲሁ በነጻ ተሰናብተዋል። 

የፌደራል ዐቃቤ ህግ በስድስተኛ ተከሳሽ ላይ ያቀረበው ክስ “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በስልጣን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል [ፈጽመዋል]” የሚል ነበር። ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው ችሎት ግን ዐቃቤ ህግ “እንደ ክስ አቀራረብ በበቂ ሁኔታ ያላስረዳ መሆኑን” በመጥቀስ ተከሳሹን በነጻ አሰናብቷቸዋል። ተመሳሳይ ብይን የተሰጣቸው አስራ አንደኛ ተከሳሽ ጉዳያቸው ሲታይ የነበረው በሌሉበት ነበር። 

በሌላ በኩል ችሎቱ ጉዳያቸውን በሌሉበት ሲታይ በነበሩ አስረኛ ተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል። እኚህ ተከሳሽ “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ነበሩ። ይኸው ክስ የቀረበባቸው ቀሪ አምስት ተከሳሾች ግን ክሱ የቀረበበት ድንጋጌ ተቀይሮላቸው እንዲከላከሉ ችሎቱ በይኗል።

የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎቱ ድንጋጌውን እንዲቀየር ብይን የሰጠው፤ “ተከሳሾቹ ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ያላቸው ባለመሆኑ” ምክንያት ነው። ብይኑ የሚመለከታቸው አምስቱ ግለሰቦች፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ከባለሙያ እስከ ዳይሬክተር ኃላፊነት ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። ችሎቱ የተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲቀየር ብይን ከመስጠቱ በፊት ቀርቦባቸው የነበረው ክስ፤ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በ2007 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ እና የወንጀል ህጉን መሰረት ያደረገ ነበር።  

በተከሳሾቹ ላይ ተጠቅሶ የነበረው አዋጅ፤ ስልጣንን አላግባብ በመገልገል የሚፈጸሙ ከባድ የሙስና ወንጀሎች እና የሚያስከትሉትን ቅጣት የሚያትት ነው። አምስቱ ተከሳሾች ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ያላቸው አለመሆኑን ያነሳው ችሎቱ፤ በወንጀል ህጉ እና አዋጁ ላይ በሰፈረው ቀላል የሙስና ወንጀል ብቻ እንዲከላከሉ ብያኔ ሰጥቷል። ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ የተበየነበት የወንጀል ህግ ድንጋጌ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ መሆንን የሚመለከት ነው። 

በተቀየረው ድንጋጌ መሰረት ተከሳሾቹ በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ከተባሉ፤ ከአንድ ዓመት የማያንስ ቀላል እስር ወይም ከ10 ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እስራት ይጠብቃቸዋል። ቀደም ሲል በዐቃቤ ህግ ቀርቦ የነበረው ድንጋጌ፤ ከሰባት ዓመት እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ10 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣትን ያዘለ ነበር።

የፌደራል ዐቃቤ ህግ ባለፈው መስከረም ወር በከፈተው የክስ መዝገብ ያቀረበው ሶስተኛ ክስ፤ “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ የወንጀል ድርጊት” ነበር። ይህ ክስ ከቀረበባቸው ስድስት ተከሳሾች መካከል ሁለቱ በዛሬው የችሎት ውሎ ነጻ ሲባሉ፤ አራቱ ደግሞ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል። 

ዐቃቤ ህግ ክሱን መስርቶ የነበረው፤ የወንጀል ህጉን እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በመጥቀስ ነው። ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ዐቃቤ ህግ ከባንኮች ያቀረባቸውን የገንዘብ ዝውውሮች እና የባንክ ሂሳብ መግለጫዎች የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ድንጋጌውን ቀይሮታል። በዚህም መሰረት አራቱ ተከሳሾች፤ በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን በሚመለከተው የአዋጁ ድንጋጌ ይከላከላሉ። 

ፍርድ ቤቱ የዛሬውን የችሎት ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት ሁለት ትዕዛዞችን ሰጥቷል። የመጀመሪያው ትዕዛዝ፤ “በነጻ የተሰናበቱት ግለሰቦች በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዙ ሲጻፍ እንዲለቅቃቸው” የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ተከሳሾች “ያላቸውን ሰው እና የሰነድ ማስረጃ እንዲያቀርቡ” የሚያዝ ነው። 

የተከሰሱበት የወንጀል ድንጋጌ ተቀይሮ እንዲከላከሉ በችሎቱ የተበየነባቸው ተከሳሾች፤ በጠበቆቻቸው በኩል የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ጠይቀዋል። የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡት ጥያቄ፤ “የተቀየረው ድንጋጌ የደንበኞቻቸውን የዋስትና መብታቸውን የማያስነፍግ በመሆኑ ዋስትና ይፈቀድላቸው” የሚል ነው። ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የሁለት ተከሳሾችን ዋስትና መብት ተቃውሞ አስተያየቱን ለችሎት አሰምቷል።

ሁለቱ ተከሳሾች “በዋና ወንጀል አድራጊነት” እና “በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ” እንዲከላከሉ የተባሉ ናቸው።  ዐቃቤ ህግ የእነዚህን ተከሳሾች የዋስትና ጥያቄ የተቃወመው፤ “ጥፋተኛ ከተባሉ ቅጣቱን ፈርተው ላይቀርቡ ይችላሉ” በሚል ነው። የተከሳሽ ጠበቆች ይህን የዐቃቤ ህግን መቃወሚያ፤ “በማስረጃ ያልተደገፈ ከመላምት ያለፈ አይደለም” ሲሉ ነቅፈውታል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ ዛሬ ከሰዓት በሰጠው ውሳኔ በተደራራቢ ክስ እንዲከላከሉ የተባሉትን ሁለት ተከሳሾች በ80 ሺህ ብር፤ ቀሪዎቹን ሶስት ተከሳሾች ደግሞ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]