በሃሚድ አወል እና በአማኑኤል ይልቃል
“አራት ኪሎ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፤ ዛሬ አመሻሽ ላይ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ተይዞ መወሰዱን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ስለ ጋዜጠኛው መያዝ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል። ጋዜጠኛው የስራ አመራር ቦርድ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበርም በተመሳሳይ ስለ ዳዊት መያዝ እስካሁን መረጃ እንደሌለው አስታውቋል።
ጋዜጠኛ ዳዊት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 4፤ 2015 አመሻሽ ላይ በመከላከያ ሰራዊት አባላት የተያዘው፤ በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው ሆምላንድ ሆቴል ከጓደኞቹ ጋር “ሻይ እየጠጣ” ባለበት መሆኑን የዓይን እማኞቹ ገልጸዋል። ጋዜጠኛውን ወዳልታወቀ ቦታ የወሰዱት የመከላከያ ሰራዊት የኮማንዶ አባላት በሁለት “ፓትሮል” ተጭነው የመጡ መሆናቸውን የጠቆሙት የዓይን እማኞቹ፤ ከእነርሱ ውስጥ አንዱ “አንተን እንፈልግሃለን” ብሎ ዳዊትን ይዞት ወደ ተሽከርካሪዎቹ እንደወሰደው አብራርተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባሉ ዳዊትን ከጓደኞቹ “ነጥሎ” ከወሰደው በኋላ፤ ከሆቴሉ ቅጥር ግቢ ውጭ ከቆሙት ተሽከርካሪዎች ወደ አንደኛው ውስጥ ሲገባ መመልከታቸውንም እማኞቹ አስረድተዋል። ሆኖም በሰዓቱ “ተደናግጠው ስለነበር” በተሽከርካሪዎቹ ውስጥ ያሉት የመከላከያ ሰራዊት አባላት አጠቃላይ ቁጥር ማወቅ አለመቻላቸውንም አክለዋል። ጋዜጠኛው በመከላከያ ሰራዊት ተይዟል መባሉን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ ስለጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ዳዊት በጸጥታ ኃይሎች ተያዞ መወሰዱ ከተነገረ ጀምሮ ባሉት ሁለት ሰዓታት ውስጥ የተንቀሳቃሽ ስልኩ ጥሪ እንደማይቀበል “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጣለች። የጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ መወሰዱ የተሰማው፤ “አራት ኪሎ ሚዲያን” ጨምሮ ሶስት የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን የሚገለገሉበት ቢሮ “ባልታወቁ አካላት” መዘረፉ ከተገለጸ አንድ ወር ገደማ በኋላ ነው።
ሶስቱ መገናኛ ብዙሃን መጋቢት 10፤ 2015 ተካሄዷል ባሉት ዝርፊያ፤ “አራት ካሜራዎች እንዲሁም ሌሎች የቀረጻ እና የፕሮዳክሽን መሳሪያዎች” እንደተወሰዱባቸው አስታውቀው ነበር። በዕለቱ የተዘረፉት የመገናኛ ብዙሃኑ ቁሳቁሶች፤ 1.7 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመቱ እንደሆነ መገናኛ ብዙሃኑ በጋራ ባወጡት መግለጫ መጠቀሳቸው ይታወሳል።
የ“አራት ኪሎ ሚዲያን” ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ከመሰረቱ ሁለት ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ የሆነው ዳዊት፤ በዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙሃኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን፣ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን እና ቃለ መጠይቆችን ሲያቀርብ ቆይቷል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ምሩቁ ዳዊት፤ “አራት ኪሎ ሚዲያን” ከጋዜጠኛ አላዛር ተረፈ ጋር ከመመስረቱ በፊት በተለያዩ የውጭ እና ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ሰርቷል።
ዳዊት የጋዜጠኝነት ስራን የጀመረው በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ፋና ራዲዮ፣ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን እና ኢትዮ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ ለስድስት ዓመታት ሰርቷል። ዋና መስሪያ ቤቱን በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያደረገው “አል አይን ኒውስ” የተባለው የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙሃን፤ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረገ የአማርኛ ክፍል ሲያቋቁም ከጅምሩ ከተቀላቀሉት ጋዜጠኞች አንዱ ዳዊት ነበር። ጋዜጠኛው በዚህ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ለሚሆን ጊዜ በከፍተኛ ሪፖርተርነት ሰርቷል።
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር መስራቾች ውስጥ አንዱ የሆነው ዳዊት፤ በአሁኑ ወቅት የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ አባል በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል። ጋዜጠኛው፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበሩ የሚያከናውናቸውን የህዝብ ግንኙነት ስራዎችንም ሲሰራ ቆይቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)