በአማራ ክልል በተካሄዱ ተቃውሞዎች ላይ በተወሰዱ “እርምጃዎች እና ጥቃቶች”፤ ሰዎች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

የክልል ልዩ ኃይሎችን “መልሶ ለማደራጀት” በመንግስት የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል በተካሄዱ ተቃውሞዎች ላይ በተወሰዱ “እርምጃዎች እና ጥቃቶች”፤ የሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት መከሰቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። እርምጃዎቹ የተወሰዱት “በጸጥታ ኃይሎች” መሆኑን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ “ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎችም” ጥቃቶች አድርሰዋል ብሏል።

ኢሰመኮ ይህንን ያስታወቀው፤ የክልል ልዩ ኃይሎችን “መልሶ የማደራጀት” ውሳኔ እና ትግበራ “የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ ሊከናወን እንደሚገባ” ባስታወቀበት መግለጫው ነው። ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 4፤ 2015 ምሽት ላይ የወጣው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም ወደ ተግባር መግባቱን ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ተቃውሞዎችን በተመለከተ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።

የኮሚሽኑ ክትትል፤ በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሱ ግጭቶች እና ጉዳቶችን ጭምር እንደሚሸፍን መግለጫው ጠቁሟል። ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው፤ በአማራ ክልል በሚገኙት ቆቦ፣ ባህር ዳር፣ ወረታ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን እና መራዊ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች፣ የመንገድ መዘጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እንዲሁም በጸጥታ ኃይሎች መካከል ፍጥጫዎች መከሰታቸውን አመልክቷል።

“በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች፤ በጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች እና ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች፤ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ሰራተኞችን ጨምሮ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት አስከትሏል”  ብሏል ኢሰመኮ። ተቃውሞ በነበረባቸው የአማራ ክልል ከተሞች እና በሌሎችም አካባቢዎች በተፈጠረው ውጥረት፣ አለመረጋጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እና የእንቅስቃሴ እገዳዎች ምክንያት፤ በክልሉ ነዋሪዎች “የዕለት ተዕለት ኑሮ እና ስራ ላይ እንቅፋት” መፈጠሩንም ኮሚሽኑ በመግለጫው አብራርቷል።

ኢሰመኮ የልዩ ኃይል አባላትን “የመልሶ ማደራጀት” ውሳኔ በመቃወም የተከሰተው አጠቃላይ ችግር እና የጸጥታ ሁኔታ፤ “አስቸኳይ እልባት ካላገኘ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስጋት” እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል። መንግስት “የፖሊሲ ውሳኔውን አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ” ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ በትዕግስት እና በጽሞና የሚያስረዳበትን ሁኔታ እንዲያመቻች የጠየቀው ኮሚሽኑ፤ ሁሉም አካላት ጉዳዩን “በምክክር እና በመግባባት” እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል። 

በአማራ ክልል በተካሄዱ ተቃውሞዎች በሰዎች ላይ ለደረሱት ጉዳቶች፤ መንግስት “አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲያረጋግጥ” ኮሚሽኑ ጠይቋል። ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው፤ “የጸጥታ አካላት ያልተመጣጠነ እና ሕይወት የሚያጠፋ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ” እንዲሁም “ሁሉም ሰው ሃሳቡን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲገልጽ” አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]