ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንዲደረግላት ባቀረበችው ጥያቄ ላይ፤ የመንግስት እና የግል አበዳሪዎች በአፋጣኝ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ጥሪ አቀረቡ። ማልፓስ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ጋር ትላንት አርብ ሚያዝያ 6፤ 2015 በዋሽንግተን ዲሲ ከተገናኙ በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ኢኮኖሚያዊ መዛባቶችን እንዲያስወግድ” ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል።
አቶ አህመድ ሽዴ እና ዴቪድ ማልፓስ የተገናኙት በዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ ከቆየው የዓለም ባንክ እና የአይ ኤም ኤፍ “የጸደይ ጉባኤ” ጎን ለጎን ነው። የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉን የመሳሰሉ ቁልፍ ባለስልጣናት የተሳተፉበት ስብሰባ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እገዛ በምትሻው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ነው።

ከዓለም ባንክ በኩል ከፕሬዝዳንቱ ማልፓስ በተጨማሪ ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የባንኩ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋን የመሳሰሉ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። ማልፓስ ከአቶ አህመድ ጋር በትላንትናው ዕለት በነበራቸው ውይይት፤ ለደሃ አገሮች ፈታኝ የሆነው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ መነሳቱን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ “ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለመመለስ ያላት አንገብጋቢ ፍላጎት” “በሰፊው” ውይይት የተደረገበት ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል። በዚሁ ውይይት “ድርቅ፣ የውስጥ ግጭት፣ የዕዳ ጫና እና ውስብስብ መዋቅራዊ ተግዳሮቶች“ ባሉበት አውድ ውስጥ፤ “ፈጣን እና ወሳኝ የፖሊሲ ማሻሻያዎች የሚኖራቸውን ጥቅሞች” በተመለከተ ማልፓስ አጽንኦት ሰጥተው ማንሳታቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።
የዓለም ባንኩ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ መንግስት “ኢኮኖሚያዊ መዛባቶችን ማስወገድ” አለበት የሚለው እምነታቸውን በመግለጫቸው አንጸባርቀዋል። ይህን እርምጃ መውሰድ “የዋጋ ንረትን ለማርገብ እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት” እንደሚረዳ ማልፓስ ገልጸዋል። ሀገሪቱ “መንግስት መር ከሆነው የኢኮኖሚ ሞዴል” በመራቅ፣ ለንግድ ስራ ምቹ የሆነ ከባቢን ማሳደግ፣ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የበለጠ ውድድር መፍቀድ እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ እድገትን ማመቻቸት እንደሚገባትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለመመለስ እና ድህነትን ለመቀነስ ጠንካራ ማሻሻያ ሲተገብር፤ የዓለም ባንክም ተመሳሳይ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል። የባንኩ ጠንካራ እገዛ፤ ዝቅተኛ ወለድ በሚከፈልበት ብድር እና በእርዳታ መልክ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጨምሮ የበጀት ድጋፍን እንደሚያካትትም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንዲደረግላት ላቀረበችው ጥያቄ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል ያለው ሂደት ዘገምተኛ መሆኑን ከዚሁ ጋር አያይዘው የጠቀሱት ማልፓስ፤ የሀገሪቱ ጥያቄን በተመለከተ የመንግስት እና የግል አበዳሪዎቿ በአፋጣኝ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በትላንቱ ውይይት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23፤ 2013 የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበርን የተመለከተው እንደሚገኝበት ማልፓስ በመግለጫቸው አመልክተዋል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት “ያሳኳቸው መሻሻሎች” በውይይቱ ላይ መነሳቱ ተገልጿል። ማልፓስ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን “ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና” የሚፈጥሩ “ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወስዱ” ማበረታታቸውን ከውይይቱ በኋላ ባወጡት መግለጫ ጠቅሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)