በሚዲያ ጥፋት የተጠረጠሩ ታሳሪዎች በሙሉ፤ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ አሳሰበ 

በአማኑኤል ይልቃል

በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል የተጠረጠሩ ታሳሪዎች “በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” ከእስር እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ። የመንግስት የጸጥታ አካላት በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላት እንዲሁም  በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ ካተኮረ “እስር እና ማዋከብ” እንዲቆጠቡም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ኢሰመኮ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችን እና አባላትን “ዒላማ በማድረግ” እየተፈጸመ ያለን “እስር እና ወከባ” አስመልክቶ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 7፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። በእነዚህ አካላት ላይ እየተፈጸመ ያለው “እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳሳቢ” መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ስምንት ጋዜጠኞች እና አንድ የማህበረሰብ አንቂ ለእስር መዳረጋቸውን በመግለጫው አስታውቋል።

ባለፈው ረቡዕ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ የተያዘው፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር መስራችና የስራ አስፈጻሚ አባል የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በኢሰመኮ መግለጫ ላይ ከተጠቀሱ ጋዜጠኞች አንዱ ነው። የ“አራት ኪሎ ሚዲያ” መስራች እና አዘጋጅ  ከሆነው ዳዊት በተጨማሪ ገነት አስማማው፣ አራጋው ሲሳይ፣ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ጌትነት አሻግሬ፣ በየነ ወልዴ፣ ሰናይት አያሌው እና ሳሙኤል አሰፋ የተባሉ ጋዜጠኞች ባለፈው አንድ ወር ለእስር መዳረጋቸውን ኮሚሽኑ ዘርዝሯል።

ባለፈው ሳምንት እሁድ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለችው “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት መስከረም አበራም በዛሬው የኢሰመኮ መግለጫ ላይ ተጠቅሳለች። በስም ከተዘረዘሩት ጋዜጠኞች ከፊሎቹ “በእስር ወቅት ተገቢ ላልሆነ አያያዝ የተዳረጉ” መሆናቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል። ከእነዚሁ ጋዜጠኞች ውስጥ የተወሰኑት “ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ እስር ተዳርገው እንደነበር” የገለጸው ኢሰመኮ፤ ከእነርሱ ውስጥ “ከተለያየ ጊዜ መጠን እስር በኋላ የተለቀቁ” እንዳሉበት ጠቁሟል።

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ክትትል ካደረገባቸው ታሳሪዎች መካከል፤ “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር የዋሉ፣ የሚዲያ አዋጁን በሚጻረር መልኩ የታሰሩ፣ በተራዘመ ቅድመ-ክስ እስር ወይም ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር የቆዩ” መኖራቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል። ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት የሚዲያ አባላት መካከል የተወሰኑት “የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው” እንደነበር ኮሚሽኑ አስታውቋል። 

ክስ ከተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል፤ ነጻ የተባሉ ወይም በዋስትና የተለቀቁ እንዳሉ ኢሰመኮ ካደረገው ክትትል መረዳቱን በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። እነዚህ የሚዲያ አባላት ከእስር የተለቀቁት፤ “ክሱ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ወይም በፖሊስ ውሳኔ ከተራዘመ እስር በኋላ” መሆኑንም ኮሚሽኑ አብራርቷል።

መንግስት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ያስታወሰው ኢሰመኮ፤ ሆኖም “በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላት እንዲሁም የማህበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚያተኩር እስር” ሌላ ውጤት እንዳያስከትል “ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ” መሆኑን አስገንዝቧል። ይህ አይነቱ እርምጃ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው፤ “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና  በህዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብቶች ላይ፤ የሚያስፈራራ፣ የሚያሸማቅቅ እና የሚገድብ ውጤት (chilling effect) እንዳይኖረው” መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል።  

ይህንን ታሳቢ በማድረግም የመንግስት የጸጥታ አካላት፤ “በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላት እና በማህበረሰብ አንቂዎች” ላይ ካተኮረ “እስር እና ማዋከብ እንዲቆጠቡ” ኢሰመኮ አሳስቧል። የጸጥታ አካላት “የተጠረጠሩ ሰዎችን ሁሉ ከምርመራ በፊት ከማሰር እንዲቆጠቡም” ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠይቋል። “በወንጀል የተጠረጠሩ እና በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በቅድመ-ክስ ሊታሰሩ የሚገባቸው ሰዎች” የሚኖሩበት ሁኔታ ሲፈጠር፤ የጸጥታ አካላት “በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በጥብቅ ጥንቃቄ” እንዲፈጽሙም ኢሰመኮ አሳስቧል። 

ለዚህም ከሁለት ዓመት በፊት የወጣውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ኢሰመኮ በማሳያነት ጠቅሷል። አዋጁ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው “ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ-ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት” መደንገጉን ኮሚሽኑ አስታውሷል። በአዋጁ አግባብ መሰረትም “በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ” ኢሰመኮ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ከኢሰመኮ ማሳሰቢያ ጋር የተመሳሰለ ጥሪ አቅርቦ ነበር። በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የሚሰሩበት “አውድ” ከጊዜ ወደ ጊዜ “እየጠበበ” መምጣቱን በመግለጫው የጠቀሰው የባለሙያዎች ማህበሩ፤ ጋዜጠኞች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ “በመንግስት የጸጥታ አካላት እየተሸማቀቁ እንግልት እየደረሰባቸው” መሆኑን መታዘቡንም አመልክቶ ነበር።  

“ጋዜጠኞች ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እየታሰሩ፣ እየታፈኑና ቤታቸው እና ቢሯቸው እየተበረበረ መሆኑ፤ ባለሙያዎች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ የፕሬስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገ ነው” ሲልም ማህበሩ በዚሁ መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። በአሁኑ ወቅት የተያዙት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የታሰሩት “ያለ ምንም የህግ አግባብ” መሆኑን የገለጸው ማህበሩ፤ መንግስት ጋዜጠኞቹን “በአስቸኳይ እንዲፈታ” እና በባለሙያዎች ላይ የሚያደርሰውን “ማሸማቀቅ እና እንግልት” እንዲያቆም ጥያቄ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]