በትግራይ ክልል “የቡድን መሳሪያዎችን የማስረከብ ሂደት” ከመጪው ሰኞ ጀምሮ እንደሚከናወን የተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

በትግራይ ክልል የሚገኙ የቡድን መሳሪያዎችን ሰብስቦ ለመከላከያ ሰራዊት የማስረከብ ሂደት በመጪው ሰኞ ሚያዝያ 9፤ 2015 እንደሚጀመር ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ሱዳን ሀገር የሚገኙ ኃይሎችን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ያሉ የትግራይ ታጣቂዎችን የማሰባሰብ ስራም በአጭር ጊዜ እንደሚጀምር ኮሚሽኑ ገልጿል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው፤ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ከተወያየ በኋላ ትላንት አርብ በሰጠው መግለጫ ነው። የተሃድሶ ኮሚሽኑን በኮሚሽነርነት የሚመሩት ተሾመ ቶጋ እና ሁለት ምክትሎቻቸው የተገኙበት ይህ ውይይት፤ በውጊያ ላይ የቆዩ ኃይሎችን “ትጥቅ የማስፈታት፣ እንዲበተኑ የማድረግ እና እንደገና ወደ ህብረተሰቡ የመዋሃድ” ሂደትን በተመለከተ “ቀሪ ስራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ” ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ተብሏል።

የቀድሞ ታጣቂዎችን እንዲበተኑ ከማድረግ በፊት መጠናቀቅ ያለበት አንዱ ስራ “ትጥቅ ማስፈታት” መሆኑን በመግለጫው የጠቀሱት ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ፤ እስካሁን የተከናወነው እንደተጠበቀ ሆኖ “የቡድን መሳሪያዎችን የማስረከብ ስራ ቶሎ መጠናቀቅ እንዳለበት” ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል። የቡድን መሳሪያዎችን የማስረከብ ሂደቱ፤ “ከሰኞ ጀምሮ በጣም ባጠረ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም” ገልጸዋል። 

የተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ መኩሪያ በበኩላቸው፤ በትግራይ ክልል እና በመከላከያ ሰራዊት የሚደረገው የቡድን ትጥቆች የመረካከብ ሂደት ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 16፤ 2015 ባሉት ጊዜያቶች ለማጠናቀቅ ከመግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል። የቡድን መሳሪያዎች የሚባሉት “ቡድን፣ ኃይል፣ ሻምበል አሊያም ሻለቃ” በተሰኙ ወታደራዊ አደረጃጀቶች ደረጃ የሚያዙ እንደ መትረየስ፣ ዲሽቃ፣ ላውንቸር የመሳሰሉ የጦር መሳሪያዎች መሆናቸውን ለወታደራዊ ጉዳዮች ቅርበት ያላቸው አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

እንደዚህ አይነት የቡድን መሳሪያዎች በነፍስ ወከፍ ደረጃ ከሚያዙ የጦር መሳሪያዎች፤ በተኩስ አቅምም ሆነ በሚሸፍኑት ረዘም ያለ ርቀት የሚለዩ መሆናቸውን እኚሁ ምንጭ አስረድተዋል። እንደ መድፍ፣ ታንክ፣ ጸረ-ታንክ፣ የአየር መቃወሚያ፣ ሚሳኤል ያሉት የጦር መሳሪያዎች ደግሞ “ከባድ መሳሪያ” በሚለው ምድብ የሚካተቱ መሆናቸውን ዘርዝርዋል። ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ በትላንቱ መግለጫቸው፤ በደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት መሰረት፤ የከባድ መሳሪያዎች የማስረከብ ሂደቱ ቀደም ሲል መከናወኑን አስታውሰዋል። 

በዚህ ርክክብ ውስጥ የአየር ኃይል ትጥቆች ጭምር እንደነበሩበት የተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል። “ብዙ ጊዜ የማይገለጸው የአየር ኃይል ትጥቅ ነው። ግን በርከት ያለ ትጥቅ የነበረ፤ ክልሉ ሰብስቦ በስነ ስርዓት ለመከላከያ ያስረከበው ትጥቅ አለ። … መከላከያ በተሟላ መንገድ የአየር ኃይል ባለሙያዎች ልኮ ርክክብ ተደርጓል” ሲሉም ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ጥቅምት 23፤ 2015 በፕሪቶሪያ ከተማ በተፈረመው ግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት፤ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የማስፈታት ሂደት ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር ነው። የጦር መሳሪያዎችን የማስፈታቱ ሂደት፤ የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የጦር አዛዦች ከሚያደርጉት ስብሰባ፤ አስር ቀናት በኋላ ሊከናወን እንደሚገባ በግጭት ማቆም ስምምነት ስድስተኛ አንቀጽ ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ ስምምነት መፈረም አንድ ሳምንት በኋላ በኬንያ ናይሮቢ የተገናኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ የግጭት ማቆሙን ተግባራዊ የሚያደርግ ስምምነት ተፈራርመዋል። ቀላል የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ አጠቃላይ ሂደት፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመ በ30 ቀናት ውስጥ ሊጠናቀቅ ከስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም፤ ሂደቱ ከአራት ወራት በኋላም አልተጠናቀቀም። 

“የቡድን ትጥቅን በተመለከተ ከጠቅላላው ታጣቂ ምዝገባ እና ከdemoblization ስራ ጋር የሚያያዝ ነው ሆኖ የነበረው። በዚህ መሰረት እየተሰራ ነው የመጣው” ሲሉ በትላንቱ መግለጫ ያስረዱት ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ፤ የማስረከብ ሂደቱን ለማከናወን አስቀድሞ “መነጋገር” እና “ትጥቆችን ወደ ተለያዩ ቦታዎች ማሰባስብ” ያስፈልግ እንደነበር አስገንዝበዋል። “ትጥቅ ሲሰበሰብ በጥንቃቄ፣ በመመካከር ነው የሚሆነው እና ይሄ ስራ እየተሰራ እንደቆየ ተረድተናል” ሲሉም አክለዋል።

በአንድ ሳምንት ውስጥ “ይጠቃለላል” የተባለው የቡድን መሳሪያ የማስረከብ ሂደትን ተከትሎ የሚከናወነው፤ “የነፍስ ወከፍ ትጥቅ የመመዝገብ እና የማስተዳደር” ስራ መሆኑን የተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል። ለምዝገባ ሂደቱ እና በስተኋላ ላይ ለሚደረገው ታጣቂዎችን የመበተን ስራ እንዲረዳም፤ “በተለያየ ቦታ ያሉትን የቀድሞ ታጣቂዎች የማሰባሰብ እና ለስራ በሚመች መንገድ ማደራጀት” በአጭር ጊዜ እንደሚጀመርም ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ በትላንቱ መግለጫቸው አመልክተዋል። ይህ የማሰባሰብ ስራ “በሱዳን አካባቢ ያለው ኃይልንም” እንደሚጨምርም ተናግረዋል።  

“ጠቅላላ ተዋጊውን ኃይል እና የያዘውን የነፍስ ወከፍ ትጥቅ” የመመዝገብ ሂደት የሚፈጸመው፤ ታጣቂዎች “በያሉበት” እንደሚሆን ከመግባባት ላይ መደረሱንም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። ከዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው፤ የምዝገባ ሂደቱን ለማከናወን “ከሚወስደው ጊዜ እና ከሚያስፈልገው ሀብት አንጻር” ተመዝኖ መሆኑንም አስረድተዋል። ከቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰበሰበው የነፍስ ወከፍ ትጥቅ ከተመዘገበ በኋላ፤ በክልሉ የሚደራጀው መደበኛ ፖሊስ እና የአካባቢ ሚሊሺያ “እንዲታጠቀው” እንደሚደረግም ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ  ገልጸዋል። ይህ የሚሆነው ግን የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በሚያደርገው ንግግር መሰረት መሆኑን አስታውቀዋል። 

ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር ውይይት ካደረጉት የትግራይ ክልል አመራሮች አንዱ የሆኑት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፤ “ከቡድን መሳሪያ ጋር በተያያዘ ያሉትን [ቀሪ] ስራዎችን በአጠረ ጊዜ አጠናቅቆ” ታጣቂዎችን ወደ መበተን እና መልሶ ከህብረተሰቡ ጋር ወደ መዋሃድ “በፍጥነት መገባት” እንዳለበት አሳስበዋል። “Demobilized የሆኑ የሰራዊት አባላት ወደ ህብረተሰቡ ሲመለሱ፣ በተገቢው መልሶ የሚቋቋሙበትን ሁኔታ የመስራት ኃላፊነት ትልቅ እንደሆነ እንገነዘባለን” ያሉት ጌታቸው፤ በዚህ ሂደት ረገድ ሊመጡ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከፌደራል መንግስት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት እንሰራለን ብለዋል።    

የቀድሞ ተዋጊ ኃይሎችን “የመበተን እና ከህብረተሰቡ ጋር መልሶ መዋሃድ” ጋር በተያያዘ “በትግራይ ጥሩ ልምድ የለም” ያሉት የክልሉ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር፤ ለዚህም ከ1983 ዓ.ም. እና ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ የተካሄዱትን ተመሳሳይ ሂደቶች በማሳያነት ጠቅሰዋል። አሁን የሚደረገው እንቅስቃሴ በተቻለ መጠን ከዚህ ቀደም የተሰሩ “ስህተተቶችን የሚያርም ሆኖ እንዲጠናቀቅ” መሆን እንዳለበት በአጽንኦት አንስተዋል። ለዚህም እንዲረዳ “በጋራ እያቀዱ፣ በጋራ መጠናቀቅ ያለባቸውን ስራዎች እያጠናቀቁ፣ በየጊዜው መገምገም” አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)