በአማኑኤል ይልቃል
በትግራይ ክልል መንግስት ስር ባሉ መዋቅሮች ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞች፤ በአስር ቀናት ውስጥ በየመስሪያ ቤቶቻቸው ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ተላለፈ። በክልሉ ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች፤ ውዝፍ የሶስት ወር ደመወዝ ክፍያ መሰጠት መጀመሩም ተገልጿል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የትግራይን ክልልን ተቆጣጥሮ የቆየው የመከላከያ ሰራዊት፤ የመቐለ ከተማን ለቅቆ ከወጣበት ከሰኔ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የክልሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች መደበኛ ስራ አቁመው ቆይተዋል። በውጊያ ላይ የቆዩት የቀድሞው የክልሉ መንግስት አመራሮች እና ኃላፊዎች ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት የክልል ቢሮዎችን እና መዋቅሮችን ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት ቢያደርጉም፤ በክልሉ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ ስራዎቻቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ሰብለ ካህሳይ፤ መደበኛ ስራ ተቋርጦ በቆየበት ጊዜ የክልሉ መንግስት ሰራተኞች በመስሪያ ቤቶቻቸው ይገኙ የነበረው ወጥ ባልሆነ ሁኔታ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ፕሮግራም ወጥቶ ነበር ሰራተኛ ወደ ቢሮ ይገባ የነበረው። በሳምንት አንድ ቀንም [የሚገባ ነበር]። አንዳንድ ስራ የበዛበትም፤ ግማሽ ግማሽ ቀን ነው ስራ ይገባ የነበረው” ሲሉ ላለፉት አንድ ዓመት ከስምንት ወር ገደማ የነበረውን የስራ ሁኔታ አስረድተዋል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መሰረት ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙን ተከትሎ፤ ሰራተኞችን በመደበኛ ሁኔታ ወደ ስራ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል። የትግራይ ክልል መንግስት 131 ሺህ ገደማ ሰራተኞች እንደነበሩት የሚናገሩት ወ/ሮ ሰብለ፤ ከእነዚህ ውስጥ በጦርነቱ ወቅት ውጊያ ላይ የነበሩ እና “በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በየቦታው የተበታተኑ” መኖራቸውን አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለ21 ወራት ደመወዝ ላልተከፈላቸው የክልሉ መንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ መፈጸም መጀመሩ፤ ሰራተኞችን ወደ መደበኛ ስራ የመመለሱ እንቅስቃሴው አንድ አካል መሆኑን ወ/ሮ ሰብለ ጠቁመዋል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከትላንት ሰኞ ሚያዝያ 9፤ 2015 ጀምሮ ክፍያ መፈጸም የጀመረው፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ልዑካን ጋር ባለፈው ሳምንት በመቐለ ከተማ ተገኝተው ካደረጉት ውይይት በኋላ ነው።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከገንዘብ ሚኒስቴር ልዑካን ጋር ካደረገው ከዚህ ውይይት በኋላ፤ የፌደራል መንግስት የድጎማ በጀት በቀናት ውስጥ እንደሚለቀቅ ይፋ መደረጉ አይዘነጋም። ይህንን ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በመዋቅሩ ስር ላሉ ሰራተኞች፤ ከዚህ ዓመት ጥር እስከ መጋቢት ድረስ ያለውን የሶስት ወር ደመወዝ መክፈል መጀመሩን የትግራይ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
አንዳንድ የክልሉ መስሪያ ቤቶች በበጀት እጥረት ምክንያት የሁለት ወር ደመወዝ እየከፈሉ መሆኑን ወ/ሮ ሰብለ ጨምረው ገልጸዋል። “በጀት ላይበቃ ይችላል። በጀቱ ቀስ በቀስ ከፌደራል ጋር እየተረዳዳን ቀስ በቀስ የሚመጣ ነው የሚሆነው” ብለዋል። የፌደራል መንግስት የ2015 ዓመትን በጀት ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ባጸደቀበት ወቅት፤ ለትግራይ ክልል 12.42 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ መመደቡን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከደመወዝ ክፍያ በተጓዳኝ፤ በመዋቅሩ ስር ያሉ ሰራተኞችን ወደ መደበኛ ስራ የሚመለሱበትን ሁኔታ አንዱ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን አመራሮች ጋር በመቐለ ከተማ ተገናኝተው የተወያዩት አቶ ጌታቸው ረዳ “ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተቋቁሞ ወደ ተሟላ ስራ ለመመለስ፤ ሰራዊት ውስጥ የገቡ፣ በተለያየ ደረጃ የመንግስት ስራ ውስጥ፣ የተለያየ የግል ሴክተርም ውስጥ የተሰማሩ ሰዎችን፤ ወደ መደበኛ ኑሯቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ በፍጥነት መስራት አስፈላጊ ነው የሚሆነው” ሲሉ ተደምጠው ነበር።

በክልሉ የተለያዩ መዋቅሮች ስር ያሉ ሰራተኞችን ወደ መደበኛ ስራ ለመመለስ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩ ተነግሯል። የትግራይ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ይህንኑ ለማከናወን የሚረዳ መመሪያ አዘጋጅቶ ለዞን፣ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች ያሰራጨው ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ መሆኑ ወ/ሮ ሰብለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በተለያዩ ደረጃ ላይ ያሉ የክልሉ መንግስት መዋቅሮች፤ መመሪያው ከደረሳቸው ጊዜ ጀምሮ በአስር ቀን ውስጥ ሰራተኞቻቸው በየመስሪያ ቤቶቻቸው ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ በመመሪያው መታዘዙንም አክለዋል።
በዚህም መሰረት አብዛኛዎቹ መስሪያ ቤቶች ከትላንት ሰኞ ሚያዝያ 9፤ 2015 ጀምሮ ለሰራተኞቻቸው ጥሪ ማድረግ መጀመራቸውን ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል። “የዚህ ማስታወቂያ [ቀነ ገደብ] ካለቀ በኋላ በተቻለ አቅም ሁሉም ሰው ይገባል ብለን ነው የምንጠብቀው። ከአቅም በላይ በሆኑ አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነርሱ ምክንያታቸውን እያቀረቡ፤ ጉዳያቸውን ኬዝ በኬዝ [እንመለከተዋለን]” ብለዋል።
የአስር ቀኑ ይህ ቀነ ገደብ በጦርነቱ ሲሳተፉ ቆይተው በካምፖች ውስጥ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን እንደማይመለከት ወ/ሮ ሰብለ አስረድተዋል። የቀድሞ ተዋጊዎቹ በፌደራል መንግስት በሚከናወነው “ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተን እና እንደገና ወደ ህብረተሰቡ የመዋሃድ ሂደትን” አልፈው “በይፋ እስከሚመጡ” እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። ይህን ስራ እንዲያከናውን ኃላፊነት የተሰጠው ለብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ነው። በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት ባለፈው ህዳር ወር የተቋቋመው ኮሚሽኑ “ለቀድሞ ተዋጊዎች አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት ለስራ ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረግ” ኃላፊነት እንዳለበት በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ተደንግጓል።

የትግራይ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ባወጣው መመሪያ፤ በውጊያ ምክንያት አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰራተኞችን ምደባ የተመለከተ አዲስ አሰራር ማካተቱን ወ/ሮ ሰብለ ገልጸዋል። በአዲሱ መመሪያ መሰረት፤ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰራተኞች “በተቻለ አቅም” የህክምና አገልግሎት ወደሚያገኙበት ቦታ ዝውውር ይደረግላቸዋል። “በፊት ዝውውር የሚደረገው ቦታ ሲገኝ ነበር። አሁን ቦታ ባይገኝም እነሱ የነበሩበትን ቦታ ሌሎች ሰዎች ደርበውም ቢሆን እንዲሰሩ በማድረግ እነሱ እንዲዛወሩ አድርገናል” ሲሉ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነሯ አዲሱን አሰራር አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)