የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ ወደ ትግራይ ለመጓዝ የያዙት እቅድ በኢትዮጵያ መንግስት ውድቅ በመደረጉ “ክፉኛ ተበሳጭተው” እንደነበር “ዋሽንግተን ፖስት” ጋዜጣ የተመለከተው አንድ ምስጢራዊ ሰነድ አጋለጠ። የዋና ጸሀፊው ጥያቄ በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት አለማግኘቱን በመግለጽ ለጉተሬዝ ደብዳቤ የጻፉላቸው፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መሆናቸው በዚሁ ምስጢራዊ ሰነድ ይፋ ተደርጓል።
ጉተሬዝ የትግራይ ጉብኝታቸው መሰረዙን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የነበሯቸውን መስተጋብሮች የያዙት ምስጢራዊ ሰነዶች አፈትልከው የወጡት ከአሜሪካ መንግስት እጅ ነው። “ዲስኮርድ” በተሰኘው የመልዕክት መለዋወጫ “ሰርቨር” የተለቀቁትን እነዚህን ሰነዶች ያወጣው፤ የማሳቹሴትስ የአየር ኃይል ብሔራዊ ዘብ ባልደረባ የነበረ የ21 ዓመት ወጣት ነው።
አሜሪካ “በወዳጆቿ እና አጋሮቿ ላይ ስታካሄድ የቆየችውን ስለላ ያጋለጡ ናቸው” ከተባለላቸው ሰነዶች መካከል አራቱ፤ ከጉተሬዝ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን “ዋሽንግተን ፖስት” ትላንት ሰኞ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል። በሰነዶቹ የተካተቱ ይዘቶች፤ የተመድ ዋና ጸሀፊ የተናገሯቸውን እና የእርሳቸው ረዳቶች ያሉትን በቀጥታ የሚጠቅሱ እንዲሁም የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት ስለ ጉተሬዝ ስሜቶች የሰጧቸውን ትንተናዎችን የቀላቀሉ እንደሆነ የጋዜጣው ዘገባ አመልክቷል።
የተመድ ዋና ጸሀፊ በቅርብ ጊዜ ካካሄዷቸው ብርቱ የዲፕሎማቲክ ጥረቶች ውስጥ፤ የትግራይ እና የዩክሬን ጦርነትን የተመለከቱቱ በእነዚህ ሰነዶች ውስጥ በአጽንኦት መነሳታቸውን “ዋሽንግተን ፖስት” ዘግቧል። የካቲት 10፤ 2015 የተጠናቀረ አንድ ሪፖርትን በማሳያነት የጠቀሰው ዘገባው፤ ጉተሬዝ ወደ ትግራይ ሊያደርጉት ያቀዱት ጉዞ መሰረዙን በተመለከተ፤ በወቅቱ በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩትን ታዬ ታዬ አጽቀስላሴን ለመጋፈጥ ፈልገው እንደነበር አትቷል።
ጉተሬዝ ወደ ትግራይ ሊያቀኑ አቅደው የነበረው፤ በክልሉ የነበረውን ጦርነት ላስቆመው የሰላም ስምምነት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ነበር ተብሏል። የተመድ ዋና ጸሀፊ የካቲት 11 እና 12፤ 2015 በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከተካፈሉ በኋላ ትግራይን ለመጎብኘት ወደ ስፍራው እንደሚበሩ “ሪፖርተር” ጋዜጣ የዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።
እንደ “ዋሽንግተን ፖስት” ዘገባ ከሆነ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ እቅድ የተጨናገፈው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጉብኝቱን ውድቅ የሚያደርግ ደብዳቤ ከላኩላቸው በኋላ ነው። ጉተሬዝ በዚህ ደብዳቤ “ክፉኛ መበሳጨታቸውን” የሚገልጽ መልዕክት በአምባሳደር ታዬ በኩል ለአቶ ደመቀ እንዲደርስ ፈልገው እንደነበር ዘገባው አመልክቷል። የተመድ ዋና ጸሀፊነትን ከተረከቡ ስድስት ዓመት ያለፋቸው ጉተሬዝ፤ በእነዚህ የኃላፊነት ዘመናቸው ከየትኛውም መንግስት ይህን መሰል ደብዳቤ አለመቀበላቸውን በአጽንኦት ማንሳታቸው በሰነዶቹ ላይ ተጠቅሷል።
ዋና ጸሀፊው፤ ይህን አይነቱ ምላሽ የያዘ ደብዳቤ ለእርሳቸው የሚቀርብበት አካሄድ “የመጨረሻ” እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል ተብሏል። አቶ ደመቀ “ከዚህ በኋላ ይህን የመሰለ ደብዳቤ የሚጽፉበት ሌላ ዕድል አይኖራቸውም” ሲሉ ጉተሬዝ መናገራቸውንም “ዋሽንግተን ፖስት” በዘገባው አስፍሯል። ይህ የተመድ ዋና ጸሀፊ ንግግር በሪፖርት መልክ በተጠናቀረበት ዕለት፤ ጉተሬዝን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመካፈል አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።
በማግስቱ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የተመድ ዋና ጸሀፊ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋርም ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ከመሪዎች ጉባኤ ጎን በተደረገው በዚህ የሁለትዮሽ ውይይት፤ በኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ስላለው መሻሻል እና ተመድ ለሀገሪቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዴት ይበልጥ ማጎልበት ይቻላል የሚሉት ጉዳዮች መነሳታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ከአዲስ አበባው የመሪዎች ጉባኤ መጠናቀቅ ማግስት፤ ጉተሬዝ ለተመድ ባለስልጣን የተናገሩትን የያዘው ምስጢራዊ ሰነድ ግን “የትግራይ ጉዞ ጉዳይ” በሁለትዮሹ ውይይት ላይ ተነስቶ እንደነበር አመልክቷል። በዚህ ውይይት ላይ፤ “ጉተሬዝ ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ በመከልከላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል” ሲል ሰነዱን የተመለከተው “ዋሽንግተን ፖስት” ዘግቧል።
የተመድ ዋና ጸሀፊ በግል ያደረጓቸውን እነዚህን ንግግሮች የአሜሪካ መንግስት በመሰለል ያገኝ እንደነበር ምስጢራዊ ሰነዱ ማጋለጡ፤ የመንግስታቱ ድርጅት ስጋቱን እንዲገልጽ አድርጎታል። የተመድ ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪች ትላንት ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ “እንዲህ አይነት ድርጊቶች፤ የመንግስታቱ ድርጅት በተቋቋመበት ቻርተር የተሰጡትን ጥቅሞች እና መብቶችን ለማስከበር፤ አሜሪካ ከገባቸው ግዴታ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው” ብለዋል። ምስጢራዊው ሰነድ ይፋ ያደረገውን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ያለው ነገር የለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)