የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ በመስከረም አበራ ላይ 10 ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ፈቀደ

በሃሚድ አወል

“ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ተጠርጥራ ከሁለት ሳምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋለችው መስከረም አበራ ላይ አስር የምርመራ ቀናት በፍርድ ቤት ተፈቀደ። “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም፤ “ረዣዥም የጊዜ ቀጠሮ የሚጠየቅብኝ ወጥቼ የጋዜጠኝነት ስራዬን እንዳልሰራ ነው” ስትል ለፍርድ ቤት ተናግራለች። 

የመስከረምን ጉዳይ እየተመለከተ የሚገኘው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ፖሊስ ባለፈው የችሎት ውሎ በተፈቀዱለት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማድመጥ ነበር። በዚህም መሰረት፤ የፌደራል ፖሊስ በተሰጡት 13 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በችሎት ፊት በንባብ ባስደመጠው በዚሁ የተግባራት ዝርዝር ላይ በቀዳሚነት የተጠቀሰው፤ “ከተጠርጣሪዋ እጅ ተያዙ” በተባሉ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ላይ ተደርጓል የተባለው ምርመራ ነው። የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎቹ እንዲመረመሩ “ለሚመለከተው መስሪያ ቤት” ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ውጤቱን መቀበሉን እና “ቀሪ የምርመራ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ” ፖሊስ በዛሬው ችሎት ገልጿል።

የመስከረምን “የገንዘብ እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ” ለባንኮች ጥያቄ ማቅረቡን ፖሊስ በተከታይነት አንስቷል። ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን እና ከሚመለከታቸው “ባለድርሻ አካላት”፤ ሌሎች ማስረጃዎች ለማግኘትን በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡንም መርማሪ ፖሊስ ለችሎት አስታውቋል። በሂደት ላይ ካሉ ከእነዚህ ተግባራት በተጨማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት ብርበራ ማድረጉን፣ የመስከረምን የጣት አሻራ  ማስነሳቱን እንዲሁም ተጠርጣሪዋን የማነጋገር ስራ ማከናወኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። 

መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው በዚሁ ማመልከቻ ላይ “ይቀሩኛል” ያላቸውን ስራዎችንም ዘርዝሯል። ከእነዚህ ስራዎች መካከል መስከረም በተጠረጠረችበት ወንጀል የደረሱ “የንብረት፣ የሰው ሞትና የአካል ጉዳቶች”ን በተመለከተ፤ “የምስክሮችን ቃል መቀበል” የሚለው በፖሊስ ማመልከቻ በቀዳሚነት ተቀምጧል። ፖሊስ ሚያዝያ 3፤ 2015 በዋለው ችሎት፤ መስከረምን “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” እንደጠረጠራት ገልጾ ነበር። 

የምስክሮችን ቃል ለመቀበል የምርመራ ቡድን ማዋቀሩን በዛሬው የችሎት ውሎ የገለጸው ፖሊስ፤ ቡድኑን ወንጀሉ ወደ ተፈጸመበት አካባቢ ለመላክ “በጸጥታ ችግር ምክንያት” አለመቻሉን ገልጿል። “በተከሰተው ህዝባዊ የአመጽ ቅስቀሳ የደረሰውን የንብረት ጉዳት መጠን ከሚመለከተው ክልል ተቋማት አጣርቶ ውጤቱን ማምጣት” የሚለውም መርማሪ ፖሊስ “ይቀሩኛል” ካላቸው ስራዎች መካከል ተጠቅሷል። መስከረም ከተጠረጠረችበት የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ የሚፈለጉ “ግብረ አበሮች፣ አመራሮች እና የወንጀል ፈጻሚዎችን” “በቁጥጥር ስር መዋል” የሚለውም፤ በፖሊስ በቀሪ ስራነት በተጠቀሱ ዝርዝሮች ተካትቷል። 

መርማሪ ፖሊስ በማመልከቻው ማሳረጊያ ላይ “ተጠርጣሪዋ የተጠረጠረችበት የወንጀል ድርጊት ውስብስብ እና የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ፣ በህዝቡ መካከል መተማመን እንዳይኖር፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ የሚያደርግ” ነው ብሏል። ተጠርጣሪዋ “የፌደራል ስርዓቱን በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸውም በላይ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጣሱ ስርዓት አልበኝነት በሀገሪቱ እንዲሰፍን ለማድረግ” የሚሰሩ መሆናቸውንም ፖሊስ በማመልከቻው ላይ አስፍሯል። 

ፖሊስ “የምርመራ ስራውን በስፋት፣ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ” አጣርቶ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ለመላክ፤ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀዱለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። መስከረም አበራን ወክለው በችሎት የተገኙት ሁለት ጠበቆች በበኩላቸው፤ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቅድ ጥያቄ አቅርበዋል። 

ከሁለቱ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ፤ “ፖሊስ በተሰጡት 13 ቀናት ደብዳቤ ከመጻፍ ባለፈ የአንድም ምስክር ቃል አልተቀበለም” ሲሉ የምርመራ ሂደቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ጠበቃው አክለውም “ደንበኛችን ከእስር ቢወጡ ምስክሮቹ የማይታወቁ ስለሆኑ የሚፈጥሩት መሰናክል የለም” ሲሉም የመስከረም የዋስትና መብት እንዲጠበቅ አመልክተዋል። ሌላኛው ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ “ደንበኛቸው ዋስትና ቢፈቅድላቸው ግዴታቸውን አክብረው የሚቀርቡ” መሆናቸውን በማንሳት የአቶ ሄኖክን ጥያቄ አስተጋብተዋል። 

በችሎቱ የመናገር ዕድል ጠይቃ የተፈቀደላት መስከረም አበራ፤ “ረዣዥም የጊዜ ቀጠሮ የሚጠየቅብኝ ወጥቼ የጋዜጠኝነት ስራዬን እንዳልሰራ ነው” ስትል ተናግራለች። መስከረም አክላም “መንግስት በፖለቲካዊ ፖሊስ፤ ፖለቲካዊ ክስ ነው እየከሰሰኝ ያለው” ስትል ለፍርድ ቤቱ አቤት ብላለች። በችሎቱ የተገኙት መርማሪ ፖሊስ ለዚህ የመስከረም ንግግር በሰጡት ምላሽ “የፖለቲካ አስፈጻሚ አይደለንም። እኛ የፖለቲካ ፖሊስ አይደለንም። የማንም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኛ ሆነን አይደለም የምናጣራው” ብለዋል። 

መርማሪ ፖሊሱ በጠበቆች በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄም ተቃውመዋል። ተጠርጣሪዋ በዋስትና ብትወጣ “ምስክሮችን ታስፈራራለች፣ ታባብላለች የሚል ትልቅ ስጋት አለን” ሲሉም መርማሪ ፖሊሱ ለችሎቱ ተናግረዋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት 10 ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ለፖሊስ ፈቅዷል። የምርመራ መዝገቡም ከቀጠሮው አንድ ቀን በፊት በጽህፈት ቤት በኩል እንዲቀርብ አዝዟል። 

ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም፤ የችሎት ውሎ ዘገባን በተመለከተ በፖሊስ የቀረበለት አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ለፖሊስ አቤቱታ መነሻ የሆነው የችሎት ዘገባ፤ መስከረም አበራ የችሎት ውሎን በተመለከተ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባለፈው ሚያዝያ 3፤ 2015 ያወጣው ዘገባ ነው። ዘገባው “መስከረም አበራ ለ’ኢ- መደበኛ አደረጃጀቶች ወታደራዊ ስልጠና እና የተኩስ ልምምድ ስትሰጥ ነበር’ ሲል ፖሊስ ወነጀለ” በሚል ርዕስ  ለንባብ የበቃ ነበር። 

ፖሊስ ለችሎት በጽሁፍ ባቀረበው አቤቱታ፤ “ተጠርጣሪ ግለሰቧ ‘የጦር ስልጠና እና የተኩስ ልምምድ ሰጥታለች’ በማለት ያቀረብነው ክርክር አልነበረም” ብሏል። የመገናኛ ብዙሃኑን እና ዘገባውን ያዘጋጀውን ጋዜጠኛ በተጠሪነት የጠቀሰው የፖሊስ አቤቱታ፤ “ተጠሪዎች ክርክሩን በዚህ መልኩ እንዲዘግቡ አሳሳች ምክንያት አልነበረም። ይልቁንም ክርክሩን በዚህ መልኩ የዘገቡት ሆነ ብለው ሃሰተኛ ዘገባ በማሰራጨት ህብረተሰቡ በሚከናወነው የህግ ማስከበር ተግባር ላይ አቋሙ እንዲናወጥ በማቀድ እንደሆነ እናምናለን” ሲል በአቤቱታው ላይ አስፍሯል። 

የፌደራል ፖሊስ በዚሁ አቤቱታው “ተግባሩ ጥፋት መሆኑ በወንጀል ህግ አንቀጽ 451/1 ላይ ተደንግጎ የሚገኝ እና በትክክል በጥፋት የቅጣት ልክ የተቀመጠለት የህግ ጉዳይ” መሆኑን አብራርቷል። በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ “ተጠሪዎችን በችሎት ፊት በመጥራት ላቀረቡት ሃሰተኛ ዘገባ ማስተባበያ እንዲሰጡ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዲያዝ” ሲል ፖሊስ ጠይቋል። የፌደራል ፖሊስ ከዚህ በተጨማሪም፤ የወንጀል ምርመራ በማከናወን ተጠሪዎችን፣ ለህግ ለማቅረብ ችሎቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል። 

በንባብ ጭምር ለችሎቱ የቀረበውን አቤቱታ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ “የዘገባው ኮፒ ለችሎቱ እንዲቀርብ” ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል። ምርመራ ማከናወን በተመለከተ ፖሊስ ላቀረበው ጥያቄ ችሎቱ በሰጠው ምላሽ፤ “የፌደራል ፖሊስ በወንጀል ተጥርጥሯል ተብሎ የሚገመትን [አካል] ይዞ የማጣራት ስልጣን” እንዳለው ጠቅሷል። ሆኖም ፖሊስ ያቀረበው አቤቱታው “የችሎቱን ስልጣን ያላገናዘበ ነው” ሲል ሳይቀበለው መቅረቱን አስታውቋል። ፖሊስ አቤቱታ ያቀረበበትን የዘገባ ኮፒ፤ ሚያዝያ 26፤ 2015 በሚውለው ችሎት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ፍርድ ቤቱ የዕለቱን ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)