በአማኑኤል ይልቃል
በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ፤ በክልሎቹ በሚገኙ ሶስት ዞኖች ባደረገው “የቁጥጥር ስራ” “አንድም ሰው አለመሞቱን” ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ። በድርቅ ሳቢያ ከእነዚህ ሶስት ዞኖች የተፈናቀሉ 243 ሺህ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙም ተቋሙ ገልጿል።
የእንባ ጠባቂ ተቋም ይህንን ያስታወቀው፤ በድርቅ እና በጎርፍ ምክንያት ከሶስቱ ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገውን ድጋፍ አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 19፤ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ተቋሙ በቦረና፣ ዳዋ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች “የቁጥጥር ስራ” ያከናወነው፤ ባለፈው መጋቢት ወር ወደ ስፍራዎቹ በላካቸው ሶስት ቡድኖችን አማካኝነት እንደነበር ጠቅሷል።
ከመጋቢት 11 እስከ መጋቢት 25 በዞኖቹ ተሰማርተው የነበሩት ቡድኖች ትኩረት ያደረጉት፤ በድርቅ እና በጎርፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች በሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ እና እርዳታ፣ መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎቶች አሰጣጥ እንዲሁም የመልሶ የማቋቋም ስራዎች ላይ እንደነበር በዛሬው መግለጫው ላይ ተመልክቷል። በክትትሉ ውጤት መሰረት ከሶስቱ ዞኖች ውስጥ ከፍተኛው ጉዳት የደረሰው በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን መሆኑን የእንባ ጠባቂ ተቋም ዋና መስሪያ ቤት የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በቦረና ዞን ያሉ ነዋሪዎች በድርቁ ሳቢያ 1.32 ሚሊዮን እንስሳት እንደሞቱባቸው እና በአጠቅላይ 33.1 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው በክትትሉ መታወቁን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በዞኑ ውስጥ በሚገኙ 20 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ 157 ሺህ ገደማ ሰዎች እንደሚገኙም አቶ አዳነ አስረድተዋል። ይህ ቁጥር በሶስቱ ዞኖች በአጠቃላይ ተፈናቅለዋል ከተባሉት ሰዎች ውስጥ 64.4 በመቶውን የሚሸፍን ነው።
በተፈናቃዮች ቁጥር ሁለተኛ ደረጃውን በያዘው በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኘው የደቡብ ኦሞ ዞን፤ በአንድ ወረዳ ብቻ 70 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉበት የእንባ ጠባቂ ተቋም ሪፖርት አመልክቷል። በዞኑ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች በቂ ድጋፍ አለመደረጉን የተናገሩት የተቋሙ የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክተሩ፤ ይህም ድርቁ የሚያደርሰው ጉዳት እንዲባባስ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
“የደቡብ ክልል በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ እንዲደረግላቸው ለፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ምንም አይነት ምላሽ እና እገዛ አለመደረጉን በሰጡን መረጃ እና ባደረግነው ምልከታ ለመረዳት ችለናል” ብለዋል አቶ አዳነ። በዚህ ምክንያት የክልሉ መንግስት ተጎጂዎችን እያገዘ ያለው “ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት” መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በዞኑ “አመራሮችን ጭምር በእርዳታ ውስጥ ለማካተት የሚደረጉ ጥረቶች” መኖራቸው ሌላው በክትትሉ የተደረሰበት ጉዳይ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተነስቷል።

የሶማሌ ክልሉ ዳዋ ዞን በተፈናቀሉበት ነዋሪዎች ብዛት በሶስተኛነት ቢቀመጥም፤ ከቦረና ዞን ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር የሆነ እንስሳት እንደሞቱበት ዛሬ ይፋ የተደረገው የእንባ ጠባቂ ተቋም ሪፖርት አመልክቷል። በዳዋ ዞን 335 ሺህ ገደማ እንስሳት እንደሞቱ የተገለጸ ሲሆን፤ 420 ሺህ ገደማ የሚሆኑት ደግሞ አደጋ ላይ በመሆናቸው አስቸኳይ መኖ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠቁሟል። በዞኑ በቅርብ ጊዜያት ጎርፍ በመከሰቱ፤ የአካባቢውን ነዋሪዎች “ለተደራራቢ አደጋ አጋልጧል” ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሶስቱ ዞኖች ባደረገው “የቁጥጥር ስራ” በጠንካራ ጎን የተመለከተው ቀዳሚ ጉዳይ፤ “አንድም ሰው በድርቅ ምክንያት አለመሞቱን” መሆኑን የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክተሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ይሁንና ይህ የተቋሙ ምልከታ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ከተሳተፉ ጋዜጠኞች ጥያቄ አስነስቷል። በድርቅ ምክንያት “ሰዎች ስለመሞታቸው መረጃዎች መውጣታቸውን” የጠቀሱት ጋዜጠኞች፤ “ሞት የተከሰተው በእንስሳት ላይ ብቻ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት በተቋሙ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተክሌ “ተቋማችንም ባደረገው ቁጥጥር፣ ከተለያዩ አካላት ባሰባሰብናቸው መረጃዎች እንዲሁም ደግሞ በምልከታ፣ የድርቁም ይሁን የጎርፉ ተጠቂ አካላት ከነበሩት ወገኖች በቀጥታ ባሰባሰብናቸው መረጃዎች መሰረት፤ የሞተ ወይም በሰው ህይወት ላይ የደረሰ [የሞት] መረጃ ልናገኝ አልቻልም” ብለዋል። ይሁንና ተቋሙ “የቁጥጥር ስራውን” ካከናወነ በኋላ ባሉት ጊዜያት የተከሰተ የሰዎች ሞት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)