የፌደራል ፖሊስ “የፍርድ ቤቶችን ውሳኔዎች እና ትዕዛዞችን አይፈጽምም” የሚሉ ቅሬታዎች በፓርላማ ስብሰባ ላይ ቀረቡ 

በሃሚድ አወል

የፌደራል ፖሊስ፤ በፍርድ ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎች እና ትዕዛዞችን “ያለመፈጸም እና የመንጓተት አካሄድን ይከተላል” የሚሉ ቅሬታዎች በተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ቀረቡ። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለቅሬታዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አለማክበር በተቋማቸው የማይታለፍ “ቀይ መስመር ነው” ብለዋል።

ቅሬታዎቹ እና ምላሾቹ የተደመጡት፤ የፌደራል ፖሊስ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተገመገመበት ወቅት ነው። ትላንት ሐሙስ ሚያዚያ 19፤ 2015 በተካሄደ በዚሁ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ፤ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ የፌደራል ፖሊስን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል። ሪፖርቱ፤ በወንጀል መከላከል እና በወንጀል ምርመራ ረገድ የተከናወኑ ስራዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር። 

ኮሚሽነር ደመላሽ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ፤ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት እና ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ተደምጠዋል። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ከፍርድ ቤት ውሳኔ እና ትዕዛዝ አፈጻጸም ጋር የተያያዙት ይገኙበታል። አቶ አዳነ ማንዴ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች “አልፎ አልፎ ሳይፈጸሙ የሚንከባለሉ እና የሚቀሩ” መኖራቸውን ከቀረቡ ቅሬታዎች መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አዳነ፤ በፍርድ ቤቶች የስራ ግምገማ ወቅት “ካጋጠሙ ዋነኛ ችግሮች” በሚል ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ የውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመሆን አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባል ለዚህ አስረጂ ይሆናሉ ያሏቸውን የፍርድ ቤት ጉዳዮችንም በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

አካልን ነጻ በማውጣት አቤቱታ ፍርድ ቤት ዋስትና ቢፈቅድም፤ ሳይፈቱ የቀሩ የሁለት ግለሰቦችን ጉዳይ በምሳሌነት ያነሱት አቶ አዳነ፤ “እኛ ያሰባሰብናቸው ከ22 በላይ መዝገቦች አሉ” ሲሉ ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች መኖራቸውንም ተናግረዋል። “ፖሊስ ከዚህ አንጻር ምን እንደተቸገረ ለቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ ቢሰጥ?” ሲሉ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ሳይፈጸሙ “የሚንከባለሉበት እና የሚቀሩበትን” ምክንያት ጠይቀዋል። 

ሌላኛዋ የቋሚ ኮሚቴው አባል ፋናዬ መለሰም በተመሳሳይ ከፍርድ ቤት ውሳኔ አፈጻጸም ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሰንዝረዋል። “ፍርድ ቤት ቀርበው፤ ፍርድ ቤቱ ጥፋት አላገኘሁባቸውም ብሎ በነጻ ያሰናበታቸውን ግለሰቦች ፖሊስ ‘አልፈታም’ ሲል እና መልሶ ሲያስር ይስተዋላል” ያሉት ፋናዬ፤ “ጉዳዩን ዜጎች ከሚያቀርቡት ቅሬታ በተጨማሪ በፍርድ ቤቶች ላይ ባደረግነው የመስክ ምልከታ ማረጋገጥ ችለናል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።  ድርጊቱን “ህጋዊ ስርዓት ያልተከተለ ተግባር” ሲሉ የገለጹት የፓርላማ አባሏ፤ የፌደራል ፖሊስ “ፍርድ ቤት ነጻ ያለውን ተጠርጣሪ አስሮ የሚያቆይበት ምክንያት” ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ከፍርድ ቤት ውሳኔ እና ትዕዛዞች አለመፈጸም ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ የፓርላማ አባላት ብቻ አልነበሩም። ከህዝብም ተመሳሳይ ጥያቄ መነሳቱን የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ተናግረዋል። አቶ ኢሳ በንባብ ካሰሟቸው የህዝብ ጥያቄዎች መካከል፤ “ፍርድ ቤት የወሰነውን ፖሊስ እንደፈለገው ሲሽረው ይስተዋላል። ይህ ጉዳይ ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ እና በህግ አስከባሪ አካላት ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳሳ ስለሆነ መልስ ቢሰጥበት” የሚለው ይገኝበታል።

ለጥያቄዎቹ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎች፤ ከፍርድ ቤት ውሳኔ አለመፈጸም ጋር በተያያዘ የተነሳውን ወቀሳ አስተባብለዋል። ተቋሙን የሚመሩት ኮሚሽነር ደመላሽ “እኛ በጣም የምንጠነቀቀው የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ማክበር ነው፤ even እያወቅንም ቢሆን። አንዳንዱ ቀጥሎ ችግር እንደሚፈጥር እየታወቀም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “ፍርድ ቤት ያዘዘውን እኛ የማንፈጽም ከሆነ ሌላ የሚፈጽም አካል ስለሌለ፤ ይሄ በፍጹም እኛ ጋር ቀይ መስመር ነው። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከበር አለበት” ሲሉ ኮሚሽነሩ በአጽንኦት ተናግረዋል። 

በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ የሆኑት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም “የፍርድ ቤት ውሳኔ በጣም ነው የምናከብረው። በተለይ ይሄ ሪፎርም ከመጣ ወዲህ፤ ፍርድ ቤት በእኛ ላይ በየትኛውም ጊዜ ቅሬታ እና ደብዳቤ ጽፎ ጠይቆን አያውቅም” ብለዋል። ሁለቱም የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎች በምላሻቸው፤ የይግባኝ አቤቱታን በተመለከተ ተቋማቸው የሚከተለው አካሄድ ህግን የተከተለ መሆኑን ደጋግመው ገልጸዋል።   

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“በፍርድ ቤት ትዕዛዝ [ላይ] እኛም መብት አለን” ያሉት ኮሚሽነር ደመላሽ፤ “ተጠርጣሪው አደጋ ያደርሳል ብለን ስናስብ [እና] ፍርድ ቤት ሲለቅብን በየደረጃው እየቀረብን እናመለክታለን” ሲሉ ፖሊስ የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ እንደሚል አስረድተዋል። ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም በተመሳሳይ “ከጊዜ ቀጠሮ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜ፤ ደረጃዎችን ጠብቀን እስከ ሰበር ድረስ ይግባኝ እንድንጠይቅ [ህጉ] ለእኛም ይፈቅድልናል” ሲሉ የኮሚሽነር ደመላሽን ምላሽ አጠናክረዋል። 

ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ከጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች እስር ጋር በተያያዘ ከህዝብ ለቀረበ ጥያቄም ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። በቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ በንባብ የቀረበው ጥያቄ፤ “ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች [እና] ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ ይታሰራሉ። ይሄ ነገር መቼ ነው የሚቆመው?” የሚል ነው። 

“አንዳንዶቹ ይሄን መንግስት በኃይል ለመጣል ከውጭም፣ ከውስጥም የተለያዩ አደረጃጃቶችን ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው” በማለት ምላሽ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም፤ “በጋዜጠኝነት ሽፋን ፈቃድ ወስደው የሚሰሩ አክቲቪስት ነን ባዮች እነዚህ ናቸው አብዛኛውን ስራ እየመሩ ያሉት” ሲሉ ወንጅለዋል። መንግስት “ከበቂ በላይ ትዕግስት አድርጓል” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም፤ “አትጠይቁን ነው እየተባልን እየተተቸን ያለነው” ሲሉ ከጋዜጠኞች እስር ጋር በተያያዘ ተቋማቸው የሚቀርብበትን ትችት አስተባብለዋል። “ስራዎችን እየሰራን ያለነው፤ የመናገር እና የመጻፍ ነጻነትን በማይጋፋ መንገድ ነው” ብለዋል።  

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ በበኩላቸው “እነሱ ባጠፉ ጊዜ፣ መረጃዎች ባገኘን እና ህግ ጥሰዋል ብለን ባመን ጊዜ፣ እነዚህን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እያዋልን ፍርድ ቤት ማቅረባችን ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል። በፌደራል ፖሊስ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት በተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት እጸገነት መንግስቱም፤ “እነዚህን አካላት ምንም መታገስ አያስፈልግም። በቂ መረጃ እስካለ ድረስ የህግ የበላይነት መከበር አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)