በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት “በጉልህ ጥቃት ስር” እንደሚገኝ አንድ ዳሰሳ አመለከተ 

በተስፋለም ወልደየስ

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ 29 ጋዜጠኞች በታሰሩባት ኢትዮጵያ፤ የፕሬስ ነጻነት “ጉልህ ጥቃት” እንዳጋጠመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት አስታወቁ። ባለስልጣናት የፕሬስ ነጻነትን ማፈን በሚፈልጉባቸው በምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት፤ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየጨመረ መምጣቱንም ተቋማቱ ገልጸዋል።

ሁለቱ ተቋማት ይህን ያሉት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 25፤ 2015 ታስቦ የሚውለውን የዓለም የፕሬስ ነጻነትን በማስመልከት በጋራ ባወጡት ዳሰሳ ነው። ዳሰሳው ኢትዮጵያን ጨምሮ በ10 የአፍሪካ ሀገራት ያለውን የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን እና በጋዜጠኞች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በማሳያነት በማንሳት ዳሰሳ አድርጓል። 

በምስራቅ እና በደቡባዊ አፍሪካ በጋዜጠኝነት ላይ ጥቃቶች፣ ወከባ፣ ማስፈራራት እና ወንጀለኛ የማድረግ “አሳሳቢ ዝንባሌዎች” እንዳሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቀጠናው ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ ተናግረዋል። በእነዚህ ሀገራት ያሉ ባለስልጣናት፤ የሙስና እና የሰብዓዊ መብት ውንጀላዎችን የሚያጋልጡ መገናኛ ብዙሃንን “ጸጥ እስከ ማሰኘት” ድረስ የሚጓዙ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተዘጋጁ ናቸው ሲሉም ተችተዋል። 

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ዳሰሳ ከተጠቀሱ ሀገራት፤ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በጋዜጠኞች ላይ የከፉ ጥቃቶችን በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነችው ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነች። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የ180 ሀገራትን የዓለም የፕሬስ ነጻነትን በሚመዝንበት ዓመታዊ ዝርዝር በ140ኛ ደረጃ በተቀመጠችው ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፤ ጋዜጠኞች በየጊዜው ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው፣ እንደሚታሰሩ፣ አንዳንዴም ስራቸውን እያከናወኑ ባለበት ግድያ እንደሚፈጸምባቸው በዳሰሳው ሰፍሯል። 

Journalistes En Danger” የተሰኘው  በሀገሪቱ ቀዳሚ የሆነው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ባለፈው ጥቅምት ወር ባወጣው መረጃ መሰረት፤ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ላይ ያነጣጠሩ 124 “ኬዞች” መመዝገባቸውን ዳሰሳው ጠቅሷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ 37 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን፣ በአስራ ስምንት ሌሎች ጋዜጠኞች ላይ አካላዊ ድብደባ መድረሱን እንዲሁም 17 መገናኛ ብዙሃን እና ፕሮግራሞች መዘጋታቸውን አሊያም መታገዳቸውን ዳሰሳው አትቷል።

በአሁኑ ወቅት በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፤ ከስራቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ እና በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች  እንደሚገኙም ዳሰሳው አክሏል። ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ከኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በመለጠቅ ስሟ የተጠቀሰው ኢትዮጵያ ነች። እንደ ሁለቱ ተቋማት ዳሰሳ ከሆነ በ2022 ብቻ በኢትዮጵያ 29 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ታስረዋል። ከእነዚህ ጋዜጠኞች አምስቱ “ከጠላት ጋር ተባብራችኋል” በሚል በትግራይ ባለስልጣናት የታሰሩ እንደነበሩ ዳሰሳው አመልክቷል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ታስሮ የነበረው የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂነግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይም በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ዳሰሳ ላይ ተነስቷል። “ወታደራዊ ምስጢሮችን ለማይመለከተው አካል በግልጽ በመጻፍ” እና “ሐሰተኛ ጽሁፎችን” በማሰራጨት ተከስሶ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ባለፈው ህዳር ወር በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቱን ዳሰሳው አስታውሷል። 

“ዘ ኢኮኖሚስት” ለተባለው መጽሔት የኢትዮጵያ ዘጋቢ ሆኖ ሲሰራ የቆየው የጋዜጠኛ ቶም ጋርድነር ከሀገር መባረር ሌላው በዳሰሳው የተካተተ ጉዳይ ነው። መቀመጫውን በአዲስ አበባ አድርጎ የነበረው ጋርድነርን ባለስልጣናት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ያባረሩት፤ “ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚሰራቸው ዘገባዎች ምክንያት ከመንግስት ደጋፊዎች በኦላይን ሲደርስበት የቆየን ወከባ ተከትሎ ነው” ብሏል የሁለቱ ተቋማት ዳሰሳ። 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ከጋዜጠኛው መባረር ቀናት አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ፤ ቶም ጋርድነር በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰራ የተሰጠው ፍቃድ መሰረዙን አስታውቆ ነበር። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው፤ ጋርድነር “የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር እና የአገሪቱን ህግ አክብሮ ለመስራት የገባውን ግዴታ ማክበር አልቻለም” ማለቱ ይታወሳል። “ዘ ኢኮኖሚስት” መጽሔት ከቀናት በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ የጋድርነር ፈቃድ መነጠቁን ያወገዘ ሲሆን ዘጋቢውም የሙያውን ስነ ምግባር አክብሮ የሚሰራ እንደሆነ በመግለጽ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን ውንጀላ አጣጥሏል። 

ዕውቁ መጽሔት በዚሁ መግለጫው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ “የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እየተሸረሸረ መምጣቱን” ገልጾ ነበር። በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ዳሰሳም፤ “በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት በጉልህ ጥቃት ስር ይገኛል” ሲል ተመሳሳይ ሀሳብ አስተጋብቷል። በደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ቀጠናዊ ዳይሬክተር የሆኑት ታባኒ ሞዮ “ግልጽ ለሆነ ህብረተሰብ የፕሬስ ነጻነት መሰረታዊ ነው” ባይ ናቸው። “ባለስልጣናት ሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብር ህብረተሰብ ለመገንባት ቁርጠኛ ከሆኑ፤ ጋዜጠኞችን ማስፈራራት እና ማወከብ ማቆም ይኖርባቸዋል” ሲሉ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)