በታንዛኒያው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ዙር፤ “በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ መድረስ” አለመቻሉ ተገለጸ

በኢትዮጵያ መንግስት እና ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛኒያ ሲካሄድ የነበረው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ዙር ዛሬ መጠናቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ አስታወቁ። የሰላም ንግግሩ “በአመዛኙ ገንቢ” እንደነበር የገለጹት አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ “እንደ አለመታደል ሆኖ በዚህ የውይይት ዙር ወቅት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም” ብለዋል።

አቶ ሬድዋን ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን በዘላቂነት እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ውይይቶቹን መቀጠል እንደሚያስፈልግ ማመናቸውን በትዊተር ባሰራጩት አጭር መልዕክት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በታንዛኒያ የሰላም ውይይት ማድረግ የጀመሩት ባለፈው ሚያዝያ 17፤ 2015 ነበር።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር ድርድርን ያካተተ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀደም ብለው አስታውቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ይፋ ያደረጉት፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።   

አብይ በዚሁ ንግግራቸው ድርድሩን “የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ አብዝቶ ይፈልገዋል” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ መንግስትን ወክለው በታንዛኒያው የሰላም ንግግር ሲሳተፉ የቆዩት አቶ ሬድዋን፤ ኢትዮጵያ መንግስት “በሕገ መንግስቱ እና መሰል ጥረቶች በተመሩባቸው መሰረታዊ መርሆዎች መሰረት” ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን “ቁርጠኝነት” በድጋሚ አስተጋብተዋል።

የእርሳቸውን የትዊተር መልዕክት ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፤ በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት “በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ” እንደሆነ ገልጿል። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ “ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ” የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ አስታውቋል። ሆኖም ሁለቱም አካላት በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በዘላቂነት እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል፤ “የሰላም ውይይቱ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ” ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን አክሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በበኩሉ ባወጣው አጭር መግለጫ፤ ሁለቱም ወገኖች በኦሮሚያ ክልል ያለውን “ግጭት በቋሚነት እና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አስፈላጊነት ላይ  እውቅና” እንደሰጡ አመልክቷል። በታንዛኒያ የተደረገው “የመጀመሪያ የሰላም ንግግር ሙከራ” መጠናቀቁን ያረጋገጠው ሰራዊቱ፤ በዚህኛው ዙር ውይይት “በቁልፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ” ከስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]