ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር በ16 ደረጃዎች አሽቆለቆለች 

በተስፋለም ወልደየስ

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (RSF) በዓመቱ በሚያወጣው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር፤ ኢትዮጵያ ዘንድሮ 130ኛ ደረጃ አገኘች። የ180 ሀገራት የፕሬስ ነጻነት በሚመዘንበት በዚህ ዝርዝር፤ ኢትዮጵያ አምና ከነበራት በ16 ደረጃዎች አሽቆልቁላለች። 

መቀመጫውን በፓሪስ ፈረንሳይ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ፤ ይህን የሀገራት ደረጃ ላለፉት 20 ዓመታት ሲያወጣ ቆይቷል። በየሀገራቱ ያሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አውዶች፣ የህግ ማዕቀፍ እና የደህንነት ሁኔታ፤ ድርጅቱ ደረጃዎቹን ለማውጣት በጠቋሚነት የሚገለገልባቸው መመዘኛዎች ናቸው። 

እነዚህ ጠቋሚ ሁኔታዎች፤ በጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙሃን ላይ ከሚደርሱ በደሎች ብዛት አንጻር እንደሚመዘኑ ድርጅቱ ስለ ደረጃ አወጣጡ ባብራራበት ክፍል ላይ ተቀምጧል። ድርጅቱ ለመረጣቸው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን እና የሰብዓዊ መብት ተከላካዮች ጥያቄ በማቅረብ የሚሰበስባቸው ምላሾችም፤ ለደረጃ አሰጣጡ በግብዓትነት እንደሚያገለግሉ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 25 ይፋ በተደረገው የዘንድሮው ዝርዝር ከተገመገሙ 180 ሀገራት መካከል፤ በሰላሳ አንዱ ያለው የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ “በጣም መጥፎ” መሆኑን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል። በዚህ ምድብ ውስጥ ከተካተቱ ሀገራት ውስጥ የኢትዮጵያ ጎረቤት ኤርትራ ትገኝበታለች። በ174ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውን ኤርትራን በመከተል በደረጃው ዝርዝር ላይ የተቀመጡት ሶሪያ፣ ቱርክሜንስታን እና ኢራን ናቸው። ቬትናም፣ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ እንደቅደም ተከተላቸው የመጨረሻዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘዋል።

በሀገራቸው ያለው ሁኔታ ለፕሬስ ነጻነት “መጥፎ” የሚባል መሆኑ ከተነገረላቸው 42 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ተካትታለች። በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ፤ በፈረንጆቹ 2022 ዓመት እንደነበረው ሁሉ “አስቸጋሪ” ሆኖ መቀጠሉን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል። 

“በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የተገኙ የፕሬስ ነጻነት ትሩፋቶች፤ ሀገሪቱ በብሔር ግጭት እና የእርስ በእርስ ጦርነት ከተዘፈቀች በኋላ ጠፍተዋል” ሲል ድርጅቱ አስታውቋል። ምንም እንኳ ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ የሰላም ስምምነት ቢፈረምም፤ በኢትዮጵያ ያሉ ጋዜጠኞች አሁንም ቢሆን “የበቀል እርምጃ” ይወሰድብናል ብለው እንደሚፈሩ ድርጅቱ ገልጿል።

ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የነበራት ደረጃ 114ኛ ነበር። ሀገሪቱ በዓለም የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር ከፍተኛ መሻሻል አሳይታ የነበረው በፈረንጆቹ 2019 ዓመት ነበር። ኢትዮጵያ አርባ ደረጃዎችን በአንድ ጊዜ አሻሽላ 110ኛ ላይ በተቀመጠችበት በዚያን ዓመት፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚዘጋጀውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እንዲከበር ማድረግ ችላ ነበር። የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ የምታስተናግደው፤ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ የሆነችው የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ናት። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)