በአማኑኤል ይልቃል
የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት በወላይታ ዞን በድጋሚ የሚደረገው ህዝበ ውሳኔ፤ በመጪው ሰኔ 12፤ 2015 እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ለህዝበ ውሳኔው የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው፤ ድምጽ በሚሰጥበት ቀን እንደሆነም ቦርዱ ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ይህንን ያስታወቀው በወላይታ ዞን በድጋሚ የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ፤ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 26፤ 2015 በአዲስ አበባ ሳፋየር ሆቴል እያደረገ ባለው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ነው። በዚህ ምክክር ላይ የነባሩ ደቡብ ክልል እና የወላይታ ዞን አመራሮች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚህ ውይይት ላይ በድጋሚ ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ፤ ቦርዱ ያዘጋጀውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ህዝበ ውሳኔው ከአንድ ወር ከ15 ቀናት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን ውጤቱ ደግሞ በሰኔ 19 ይገለጻል። በዚህ ህዝበ ውሳኔ 998,00 መራጮች ይሳተፋሉ የሚል ግምቱን ያስቀመጠው ቦርዱ፤ የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው በድምጽ መስጫው ዕለት ሰኔ 12 መሆኑን አስታውቋል።

የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ አሰጣጡ በተመሳሳይ ቀን የሚከናወን በመሆኑ፤ በምርጫ ጣቢያዎች ረዥም ሰልፍ እንዳይኖር ቦርዱ መፍትሔ አስቀምጧል ተብሏል። በዚህም መሰረት በአንድ ምርጫ ጣቢያ የሚስተናገደውን የመራጭ ቁጥር ከ1500 ወደ 800 ዝቅ መደረጉን ቦርዱ ገልጿል። ከዚህ ቀደም በተደረገው ህዝበ ውሳኔ በዞኑ 1,112 ምርጫ ጣቢያዎች የነበሩ ሲሆን በአሁኑ የጣቢያዎቹ ቁጥር 1,804 እንደሚሆን በምክክሩ ላይ ተነግሯል። የጣቢያዎች ማስተባባሪያ ማዕከላትም ከስምንት ወደ 11 እንዲል ተደርጓል።
የወላይታ ዞንን ጨምሮ በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች፤ አዲሱን የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት ህዝበ ውሳኔ ተካሄዶ የነበረው ከሶስት ወራት ገደማ በፊት ጥር 2015 ነበር። ህዝበ ውሳኔ ከተደረገባቸው የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ከወላይታ ዞን ውጭ ያሉት በሙሉ፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት መወሰናቸውን ምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት ወር ላይ በሰጠው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ቦርዱ በዚሁ መግለጫው፤ በወላይታ ዞን ግን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ እና የመራጮች ምዝገባ ውድቅ እንዲሆን መወሰኑንም አስታውቆ ነበር። በዞኑ የተደረገው ህዝበ ውሳኔ እና የመራጮች ምዝገባ ውድቅ የተደረገው፤ በሂደቶቹ ላይ “መጠነ ሰፊ” የህግ ጥሰቶች መፈጸሙ በምርመራ በማረጋገጡ እንደሆነ ቦርዱ ገልጿል።

በወላይታ ዞን የተፈጸሙት ጥሰቶች የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ መሆናቸውን በወቅቱ በተሰጠው መግለጫ ላይ የተናገሩት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ህዝበ ውሳኔው በድጋሚ ከመካሄዱ በፊት ተጠያቂነት መስፈን እንዳለበት አስገንዝበው ነበር። በህዝበ ውሳኔው ከተፈጸሙ ጥሰቶች ጋር በተያያዘ 92 የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የወረዳ እና የቀበሌ ኃላፊዎች፤ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የወላይታ ዞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማስታወቁ ይታወሳል።
ባለፈው ወር በቁጥጥር ስራ ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ የምርጫ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን ዞኑ ገልጾ ነበር። በሰኔው ህዝበ ውሳኔ ከዚህ ቀደም የተሳተፉ ምርጫ አስፈጻሚዎችን “ሙሉ በሙሉ” እንደማይጠቀም ምርጫ ቦርድ በዛሬው ውይይት ላይ አስታውቋል። በድጋሚ ለሚደረገው ህዝበ ውሳኔ 9,020 የምርጫ አስፈጻሚዎችን እንደሚያሰማራ ያስረዳው ቦርዱ፤ አንድ ጣቢያ ውስጥ አምስት የምርጫ አስፈጻሚዎች እንደሚኖሩ ገልጿል።
በአንድ ጣቢያ ውስጥ ከሚኖሩት አስፈጻሚዎች ውስጥ ሶስቱ ከአዲስ አበባ፤ ሁለቱ ደግሞ ከአካባቢው እንደሚመረጡ ይፋ ተደርጓል። ቦርዱ 5,400 ገደማ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ከአዲስ አበባ ለመምረጥ የወሰነው፤ “ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ጥሰቶች እንዳይደገሙ” በማሰብ መሆኑን የምርጫ ቦርድ የኦፕሬሽን አማካሪ አቶ ብሩክ ወንድወሰን አስታውቀዋል። ከአዲስ አበባ የሚመረጡ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የተሳተፉ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]