የሀገራዊ ምክክር ሂደት መዘግየት፤ በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ጥያቄ አስነሳ

በሃሚድ አወል

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመቻችነት የሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ሂደት መዘግየት፤ በተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ጥያቄ አስነሳ። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርዓያ፤ ህዝብ እና መንግስት ከኮሚሽኑ የሚጠብቀው “በጣም ከፍተኛ” መሆን “ትልቅ ተግዳሮት” እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል። 

ፕ/ር መስፍን ይህን ምላሽ የሰጡት በዋና ኮሚሽነርነት የሚመሩትን፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ባቀረቡበት ወቅት ነው። ትላንት ረቡዕ ሚያዝያ 25፤ 2015 በቀረበው በዚህ ሪፖርት፤ ከምክክር ተሳታፊዎች እና አጀንዳ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ወደ ስራ ከገባ በኋላ፤ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ከ1,711 ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች መካሄዳቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በእነዚህ ውይይቶች ግብዓቶች እና መረጃዎች የተሰበሰቡባቸው መሆኑን ፕ/ር መስፍን ተናግረዋል።  “ከትግራይ ክልል እና ከኦሮሚያ ክልል ሰባት ዞኖች ውጭ ሁሉንም ለስራ ዝግጁ አድርገናል” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ግብዓቶች ባልተሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ውይይቶች ለማካሄድ ሙከራዎች መደረጋቸውንም ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።  

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ዋና ኮሚሽነሩ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ ሲያስረዱ “ለጊዜያዊ መስተዳድሩ ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ጽፈናል። እስካሁን መልሳቸውን እየጠበቅን ነው። ከእነርሱ በኩል ይሁንታውን ካገኘን ቶሎ ብለን የትግራይንም ከሌሎቹ እኩል እንዲሄድ ነው የምናደርገው” ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል ውይይት ባልተካሄደባቸው ዞኖች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተመለከተም፤ “አዳማ ወይም ቢሾፍቱ ላይ መጥተው ስብሰባ እንድናደርግ ጥሪ አድርገናል። የሚመጡ ከሆነ ያለውን ነገር የምናካፍላቸው ነው የሚሆነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንደተግዳሮት ከለያቸው ጉዳዮች መካከል፤ ህዝቡ ከኮሚሽኑ የሚጠብቀው (public expectation) “በጣም ከፍተኛ” መሆኑ ጎልቶ የሚጠቀስ እንደሆነ ፕ/ር መስፍን ገልጸዋል። “ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ የት ደረሳችሁ? ምን ላይ ናችሁ? ለምን ዘገያችሁ? ለምን ቶሎ ቶሎ አትሉም? ‘የሰሜን ሁኔታ እንደዚህ ነው፤ ደቡብ እንደዚህ ነው’ የሚል ከፍተኛ የሆነ ጥያቄ አለ” ሲሉ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ስሜት አብራርተዋል።   

“የመንግስትም ፍላጎት ቶሎ እንድንሰራ ነው” ያሉት ፕ/ር መስፍን፤ “አንዳንድ ጊዜ ስራዎች ወደ እኛ ዝም ብለው በጫና መልክ ይመጣሉ” ሲሉ ተናግረዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አለ ያሉትን “ጫና” ሲያብራሩ “ምክክር ኮሚሽኑ ይኼን ይሰራዋል፤ ይኼን ያደርገዋል፤ ይኼን ይፈጽመዋል የሚባሉ ግፊቶችም እኛ ጋር አሉ” ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄ እና አስተያየቶቻቸውን አቅርበዋል። አባላቱ ያነሷቸው አብዛኞቹ ጥያቄዎች እና የሰጧቸው አስተያየቶች፤ በሂደቱ መዘግየት እና በተሳታፊዎች ልየታ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። እድል አግኝተው ከተናገሩ ስምንት የቋሚ ኮሚቴው አባላት መካከል አምስቱ፤ የምክክር ሂደቱን መዘግየት በጥያቄ አሊያም በአስተያየት መልክ አንስተውታል።

መስፍን እርካቤ ተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል የኮሚሽኑ አካሄድ “አዝጋሚ” መሆኑን ጠቅሰው፤ እንዲያም ቢሆን ግን ባለፉት ዘጠኝ ወራት “ጥሩ ጥሩ ስራዎች” መሰራታቸውን ተናግረዋል። ተመስገን አምባቸው የተባሉ አባልም በተመሳሳይ “ከዕቅድ ክንውን አኳያ በተለይ የአጀንዳ ልየታ ውይይት እንደሚጀመር ነበር አሁን ጠብቀን የነበረው። ኮሚሽኑም በዕቅድ አስቀምጦ የነበረው [ይህንኑ ነው]። እሱ ጋር የመዘግየት ነገር አለ ብዬ ነው እኔ የምወስደው። የሚነሳ ምክንያት ይኖራል ወይ ለመዘግየቱ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።

ሌላኛዋ የቋሚ ኮሚቴው አባል ዘሀራ ቢፍቱ በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚጠብቀው አኳያ ስናይ ትንሽ ስራዎች የተቀዛቀዙ ይመስላሉ። ለመቀዛቀዙ ምንድን ነው ምቹ ነገር ያልተፈጠረው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጠው የሶስት ዓመት ስራ ዘመን “ከአንድ ዓመት በላይ” የሚሆነውን እንዳሳለፈ ያነሱት አቡኔ አለሙ የተባሉ አባል፤ “የሆነች እርሾ ለማስቀመጥ ትንሽ ጊዜው የሄደ ስለመሰለኝ፤ ይሄን ያህል ለፍታችሁ ዳር ላይ ውጤት ላይ ለመድረስ ስጋት አይሆንም ወይ? ጊዜው አልሄደብንም ወይ?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ይህ የመዘግየት ጉዳይ በ31 ገጾች በተዘጋጀው የምክክር ኮሚሽኑ ሪፖርት ላይም ተነስቷል። “የምክክር ዝግጅት ሂደቱን አካታች እና ግልጽ ለማድረግ” የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸው በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። ተግባራት በዕቅድ ሲቀመጡ የተወሰነ ጊዜ የተበጀተላቸው መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ “ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች አንጻር ግን ለትግበራ ረዘም ያለ ጊዜያትን ወስደዋል” ሲል ሂደቱ የዘገየበትን ምክንያት አብራርቷል።

በትላንትናው የፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ከተገኙት የምክክር ኮሚሽኑ አምስት ኮሚሽነሮች አንዱ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም፤ ከሂደቱ መዘግየት ጋር በተያያዘ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ኮሚሽነሩ በምላሻቸው “በጣም reasonable time ወስደናል ባንልም፤ የሚገባውን ያህል ወስደናል” ብለዋል። “ቶሎ ቶሎ ብለን የምንገባበት አይደለም። ቶሎ ብንገባ ደግሞ ብልሽቱም የዚያኑ ያህል ነው የሚሆነው” ሲሉ ሂደቱ ጊዜን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል። 

“ይሄ ሀገራዊ ምክክር በዘመናት መካከል ተደርጎ የማያውቅ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚካሄድ ሂደት ነው። በጣም ቀላል የሆነ፤ በሁለት ሰዎች ወይም በሁለት ጎሳዎች መካከል የነበረ ግጭትን ወደ አንድ ለማምጣት የሚደረግ exercise አይደለም። ይሔ ትልቅ የሆነ ብሔራዊ ፕሮግራም ነው” ሲሉም ከመዘግየት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ አቅርበዋል። 

ኮሚሽነር መላኩ በዚሁ ማብራሪያቸው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ በሶስት ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ ከለያቸው አራት ምዕራፎች ውስጥ የቅድመ ዝግጅት እና የዝግጅት ምዕራፎችን ማጠናቀቁንም አመልክተዋል። ቀሪዎቹ ሁለት ምዕራፎች የምክክር ሂደት እና የትግበራ ምዕራፎች ናቸው። እርሳቸው ይህን ቢሉም የፓርላማው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ “በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ምን እንጠብቅ” የሚል ጥያቄ በቀጥታ ለዋና ኮሚሽነሩ አቅርበዋል። ፕ/ር መስፍን ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ “ዋናው ነገር ምንድን ነው፤ መሰረት እየጣልን መሄዳችን ነው ትልቁ ነገር” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ሌላኛው በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተደጋጋሚ የተነሳው ጥያቄ፤ የተሳታፊዎች ልየታን የተመለከተ ነው። አቶ ተመስገን አምባዬ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል ተሳታፊዎች የሚለዩበት መንገድ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ዶ/ር ሐንጋሳ አህመድ የተባሉ ሌላ የቋሚ ኮሚቴ አባል ደግሞ “በወረዳ ደረጃ ሰው ሲመለመል፤ ተመካክሮ ችግሩን ለመቅረፍ የሚፈልጉትን ሰዎች አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሐንጋሳ አክለውም “የአስተዳደሩን ችግር የማይናገር ነው የሚመረጠው። ስለዚህ ትክክለኛውን ችግር ማግኘት ላይ እንቅፋት ይሆናል” ብለዋል። ይህ አይነቱ ሂደት “በኢትዮጵያ የተለመደ ብልሹ አሰራር ነው” ሲሉ የገለጹት ዶ/ር ሐንጋሳ “ቢቻል ብሶት ያለባቸው ናቸው ወደ መድረኩ መምጣት ያለባቸው። መስፈርታችሁ ምንድን ነው?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል። 

ከተሳታፊዎች ልየታ ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ፤ “ይሄን ሂደት በከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረግን ነው ያለነው። በእኛ አያያዝ የትኛውም አካል ጣልቃ ገብቶ ያሰናክላል የሚል እምነት የለንም” ብለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚያደርገው የተሳታፊዎች ልየታ፤ ከእያንዳንዱ ወረዳ ዘጠኝ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ 18 ተሳታፊዎች ይመረጣሉ። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

እነዚህ ተሳታፊዎች በክልል ደረጃ ተገናኝተው የአጀንዳ ልየታ ላይ እንደሚሳተፉ ኮሚሽነሮቹ በትላንቱ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ገልጸዋል።ከተሳታፊዎች አጀንዳ ከተሰበሰበ በኋላ አጀንዳ የመቅረጹ ሂደት በኮሚሽኑ በኩል እንደሚከናወን ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የለያቸውን ጉዳዮች መሰረት በማድረግ የምክክር አጀንዳዎችን እንደሚቀርጽ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይም ተቀምጧል። ኮሚሽኑ የተለዩ አጀንዳዎችን ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት እንዲሁም ምክክሮችን እና ውይይቶችን የማሳለጥ ኃላፊነት እንዳለበትም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)