በአማኑኤል ይልቃል
በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በአሲዳማነት የተጠቁ መሬቶችን ለማከም በዚህ ዓመት ከሚያስፈልገው የኖራ መጠን ውስጥ፤ እስካሁን ማቅረብ የተቻለው 10.3 በመቶው ብቻ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚታረስ መሬታቸው ሙሉ ለሙሉ በአሲዳማነት እንደተጠቃም ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው፤ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ትላንት ረቡዕ ሚያዝያ 25፤ 2015 ለተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራቴጂክ እና እቅድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዜና ሀብተወልድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በአሲድ የተጠቃ መሬትን ለማከም የሚውል 1.05 ሚሊዮን ኩንታል ኖራ በተያዘው በጀት ዓመት ለማቅረብ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ማዘጋጀት የተቻለው 110 ሺህ ኩንታል ገደማ ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሲዳማ መሬትን ለማከም የያዘው እቅድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑ ከፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥያቄ አስነስቷል። ተስፋነሽ ተፈራ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፤ በሀገር ደረጃ በእርሻ መሬት ላይ እየተስፋፋ ያለውን የአሲዳማነት መጠን ለመቀነስ እና ለማከም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲሰራ የታቀደው ስራ አፈጻጸም “ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት” ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ሚኒስቴሩ ወደፊት ምን ሊሰራ እንዳሰበም እንዲገልጽ ጥያቄ አቅርበዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለእርሻ የሚውል 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ያለ መሆኑን እና ከዚህ ውስጥ 43 በመቶው በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን አስታውቀዋል። “ትርፍ አምራች” ተብሎ በሚታወቀው የሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኝ መሬት በይበልጥ በአሲዳማነት መጠቃቱን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ሙሉ በሙሉ የእርሻ መሬቶቻቸው በአሲዳማነት መጠቃታቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰር እያሱ፤ በኦሮሚያ ክልልም ችግሩ “በስፋት” እንደሚስተዋል ጠቁመዋል። የአማራ እና የደቡብ ክልሎች በምዕራባዊ ክፍሎቻቸው የሚገኙ የእርሻ መሬቶች እንዲሁ በአሲዳማነት መጠቃታቸውን ዘርዝረዋል።
በኢትዮጵያ በአሲዳማነት ከተጠቃው አጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ፤ 3.2 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው “ጠንካራ” በሚባል ደረጃ የተጎዳ በመሆኑ “ማምረት ወደማይችልበት ደረጃ” መድረሱን ሚኒስቴር ዴኤታው በዚሁ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። “ከአሲዳማነት የተነሳ ከምርት ውጪ የሆኑ በርካታ መሬቶች አሉን። ምርታማ በሆኑትም አካባቢዎች ላይ የምርት መቀነስ በከፍተኛ ሁኔታ ይታያል። 50 ኩንታል የሚሰጠው ወደ 5 ኩንታል እና ወደ ምንም ኩንታል የመስጠት አቅም ማጣት ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉ የችግሩን መጠን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።
የሚታረሱ መሬቶች በአሲዳማነት መጠቃታቸው የሚገኘው ምርት እንዲቀነስ ከማድረጉ ባሻገር፤ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙት የአፈር ማዳበሪያ የሚያስገኘው ውጤት ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ” እንደሚያደርግ ፕሮፌሰር እያሱ ገልጸዋል። የግብርና ሚኒስቴር ይህንን አስመልክቶ ባደረገው ጥናት፤ የመሬት አሲዳማነት የማዳበሪያን ውጤታማነት ከ71 እስከ 100 በመቶ እንደሚቀንስ ማረጋገጡንም አስታውቀዋል። “በብዙ ጥረት ከውጪ ያመጣነው ማዳበሪያ 71 ፐርሰንቱ ስራ ላይ የማይውል ከሆነ ለሀገር ኢኮኖሚ ምን ያህል ኪሳራ ይሆናል? ለአርሶ አደሩም ምን ያህል ኪሳራ እንደሚሆን ይሄ ቤት ማመዛዘን ይችላል” ሲሉም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
መንግስት በአሲዳማነት የተጠቃን መሬት በኖራ ማከምን መፍትሔ አድርጎ መያዙን ያስታወሱት ፕሮፌሰር እያሱ፤ “ጠንካራ” በሚባል ደረጃ የተጠቃ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በአስር ዓመት ውስጥ ለማከም መታቀዱን ተናግረዋል። ይህንን እቅድ ለማሳካት በየዓመቱ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ለዚህም በዓመት አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ይሁንና ለአሲዳማ መሬት ማከሚያ የሚውለውን ኖራ ለማቅረብ የሚያስችል ገንዘብ ባለመኖሩ ምክንያት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እቅድ አፈጻጸም አነስተኛ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል። “ባለፉት ሁለት ዓመታት ማነቆ ገጥሞናል። ይሄም መንግስት ከካዝና የሚመድበው ወደ 800 ሚሊዮን [ብር] የሚሆን ለኖራ አቅርቦት የሚውል ገንዘብ፤ በማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች እና ከውጭ የሚገባ ማዳበሪያ ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ ለዚህ ዓላማ ለማዋል ችግር ስለገጠመው፤ አቅርቦቱ ላይ ችግር ገጥሟል” ሲሉ ችግሩ በዚህ ዓመት የጀመረ አለመሆኑንም አመልክተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት እና ግብአት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ በበኩላቸው፤ አንድ መሬትን ለማከም የሚያስፈልገው የኖራ መጠን ከፍተኛ መሆን የአርሶ አደሮችን አቅም መፈተኑ ሌላ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል። አንድ ሄክታር መሬትን ለማከም እስከ 30 ኩንታል ኖራ የሚያስፈልግ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ሶፊያ፤ ለዚህም 35 ሺህ ብር እንደሚጠይቅ አስረድተዋል። አርሶ አደሮች ኖራ ለመግዛት ይህንን ያህል ገንዘብ የማውጣት አቅም እንደማይኖራቸው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ችግሩ “እንደ ሀገር ምላሽ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ” መሆኑን አስገንዘበዋል።
ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሀሳብ ያነሱት የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ፤ በመስሪያ ቤታቸው “የአፈር ለምነት ንቅናቄ” ለማስጀመር እቅድ ተዘጋጅቶ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ንግግር መጀመሩን አስታውቀዋል። የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር እያሱ፤ በዚህ እቅድ መሰረት ለኖራ አቅርቦት ስርዓት ለማበጀት መታሰቡን እና ለዚህም በጀት በልዩ ሁኔታ መመደብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር በአሲዳማነት ከተጠቁ መሬቶች የሚገኘውን ምርት ለመጨመር የሚዘሩ ሰብሎችን፤ አሲዳማነት በሚቋቋሙ እንደ ሩዝ፣ አጃ፣ ቡና እና ሻይ ቅጠል ያሉ ምርቶች ለመቀየር ጥናት እንደሚደረግ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)