ኦፌኮ የኦሮሞ ህዝብን በሚመለከቱ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ፤ “ቀሪ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ድርድር መደረግ” አለበት አለ

በሃሚድ አወል

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመንግስት እና በ“ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር ከተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈ የኦሮሞ ህዝብን በሚመለከቱ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ቀሪ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን ማሳተፍ እንዳለበት አሳሰበ። ኦፌኮ እውነተኛ እና ቀጣይነት ላለው ዕርቅ እና መግባባት ሁሉንም የፖለቲካ አመራርና ድርጅቶች ያሳተፈ “የአስተዳደር ስርዓት” መዘርጋት እንዳለበትም በአጽንኦት ገልጿል። 

ተቃዋሚ ፓርቲው ይህን የገለጸው፤ የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ለሁለት ቀናት ሲያካሄዱት የቆዩትን መደበኛ ስብሰባ ካጠናቀቁ በኋላ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 28፤ 2015 በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተጠናቀቀው፤ ሰባት የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት መሆኑ ተገልጿል።

ከሰባቱ የአቋም መግለጫዎች ሁለቱ ያተኮሩት መንግስት ከተለያዩ አማጺ ቡድኖች ጋር ሲያደርጋቸው በቆዩ የሰላም ድርድሮች ላይ ነው። የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም በንባብ ባሰሙት መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ኦሮሚያን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በአጠቃላይ እየሞከረ ያለውን እርቅ እና ድርድር” ፓርቲው “በመርህ ደረጃ” እንደሚደግፍ ያትታል፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስት እና “በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” መካከል የተፈጠረው “ጦርነት” መነሻው “ፖለቲካዊ አለመግባባት” መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤ ጦርነቱ “በሰሜን ኢትዮጵያ እንደተደረገው ሁሉ በሰላም እና በእርቅ እንዲቆም ደጋግመን ጠይቀናል” ብሏል። የኦፌኮ ተደጋጋሚ ውትወታ ተቀባይነት ሳይገኝ ቢቆይም፤ ሁለቱ ወገኖች ለመደራደር ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውን “በደስታ” የሚቀበለው መሆኑን ፓርቲው በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ድርድር በታንዛኒያ እንደሚጀምር የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ካስታወቁ ከሁለት ቀናት በኋላ የተጀመረው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ዙር፤ ከሁለት ቀናት በፊት ረቡዕ ሚያዚያ 25፤ 2015 መጠናቀቁ ተገልጾ ነበር። 

ሁለቱም ወገኖች በዚሁ ቀን በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ፤ በመጀመሪያው ዙር ውይይት “በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን” አስታውቀዋል። ሆኖም የሰላም ውይይቱ ተሳታፊዎች፤ ውይይቱን ለማስቀጠል “መግባባት ላይ መድረሳቸውን” ገልጸዋል። ኦፌኮ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫው፤ ሁለቱም ወገኖች “ቀጣዩን ድርድር በማፋጠን” ህዝቡ ለተጠማው ሰላም “ቅድሚያ እንዲሰጡ” አሳስቧል።

ኦፌኮ የሰላም ድርድሩ ውጤታማነት ላይ ያለውን ተስፋ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “ከአሁኑ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ከስድስት ወራት በፊት በፌደራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በተደረገው ስምምነት በአደራዳሪነት ተሳታፊ የነበሩት አካላት ይታወቁ እንደነበር ያስታወሱት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ “እዚህኛው ላይ በስሚ ስሚ ካልሆነ አይታወቁም” ሲሉ የሰላም ውይይቱ ዝርዝር መረጃ አሁንም ግልጽ አለመሆኑን አስረድተዋል። 

“ኢትዮጵያን ከመገዳደል ፖለቲካ እንድትሻገር የሚሞክሩ፣ የሚገፉ፣ የሚያደራድሩ፤ ጉልበትም፣ እውቀትም ያላቸው ይኑሩ አይኑሩ እርግጠኛ አይደለንም” ሲሉ በታንዛኒያው ድርድር ተሳታፊ ስለነበሩ ወገኖች ያላቸው መረጃ ውሱን መሆኑን ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል። የኦፌኮ ሊቀመንበር አክለውም “ግፊት ማድረግ የሚችሉ አደራዳሪዎች፤ ከድርድሩም በኋላ ስምምነቱ ስራ ላይ መዋሉን መቆጣጠር የሚችሉ ኃይሎች ያስፈልጋሉ” ሲሉም የሰላም ውይይቱ ውጤታማ ከሆነ በኋላ ሊደረግ የሚገባውን ጠቁመዋል። 

ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድሩ ሲመጡ “የራሳቸው ስሌት” ይዘው እንደሆነ ያመለከቱት ፕሮፌሰር መረራ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በ“ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ተወካዮች በኩል ሊነሱ የሚችሉ የድርድር ነጥቦች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። “ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ታንዛኒያ የሄደው ‘እጃችሁን ስጡ፣ መሳሪያ አስቀምጡ፣ ምህረት እናደርጋለን፣ ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ ምርጫ ይመጣል፣ ያን ጊዜ እድላችሁን ትሞክራላቸሁ’ [ብሎ] ለማባበል ይሆናል። እነዚያ ደግሞ ‘ጠመንጃ አስቀምጠን፣ ምን ዋስትና አለን? ማን ነው ዋስትና የሚሰጠን?’ የሚል ጭንቀት ያላቸው ይመስለናል” ሲሉ ስለ ድርድሩ ያላቸውን ግምገማ ለጋዜጠኞች አጋርተዋል። 

“ እንደ ሰሜኑ ድርድር ’በሁለቱ ተደራዳሪዎች መተማመን እንዲፈጠር የሚያደርግ፣ ይሄንን የሚያጠብ ሶስተኛ ወገን ያስፈልጋል’ የሚባለው ለዚህ ነው። ፕሪቶሪያ እና ናይሮቢያ ላይ እነማን ተሳታፊ እንደነበሩ፣ አገናኝ እነደነበሩ፣ አስማሚ እንደነበሩ ይታወቃሉ። አሜሪካንን የሚህል ትልቅ ጭንቅላት ከኋላ አለ። ሶስተኛ ወገን የሚባለው [የኦሮሞ ነጻነት ጦር] ሲጠይቀው የነበረው ጉዳይ ነው” ሲሉ አብራርተዋል። 

ፕሮፌሰር መረራ የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ ማድረግ የሚችሉ አደራዳሪዎችን አስፈላጊነት በዛሬው ላይ መግለጫ ላይ ደጋግመው አንስተዋል። ኦፌኮ በሁለት ገጾች ባዘጋጀው የአቋም መግለጫ ደግሞ፤ እየተካሄደ ያለው የሰላም ድርድር ስኬታማ እንዲሆን እና “በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር” ያስፈልጋሉ ያላቸውን ምክረ ሃሳቦችን በተጨማሪነት አቅርቧል። 

ፓርቲው ያቀረበው የመጀመሪያ ምክረ ሃሳብ የሰላም ድርድሩ እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ተሳታፊነት የተመለከተ ነው። ፓርቲው በመግለጫው፤ “የሰላም ድርድሩ ከተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈ፤ የኦሮሞን ህዝብ በሚመለከቱ ውስብስብ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ቀሪ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን ማሳተፍ እንዳለበት መረዳት ያስፈልጋል” ሲል በአጽንኦት አሳስቧል። እውነተኛ እና ቀጣይነት ያለው መግባባት እንዲፈጠር እና የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ፤ “ሁሉንም የፖለቲካ አመራርና ድርጅቶች ያሳተፈ የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ልንገልጽ እንወዳለን” ሲልም ኦፌኮ አቋሙን ይፋ አድርጓል።

ኦፌኮ እንዲዘረጋ የጠየቀው “የአስተዳደር ስርዓት” ምንነትን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ፕ/ር መረራ፤ ስርዓቱ “ሁሉንም የሚያሳትፍ” መሆን አለበት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “በተለይ የአሁኑ መንግስት የሽግግር መንግስት የሚለውን ለምን እንደሚጠላው አላውቅም፤ ይሸሻል። የሽግግር መንግስቱን እንተወውና ‘ሁሉን አሳታፊ መንግስት’፣ ‘ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ስርዓት’፣ ‘ብሔራዊ የአንድነት መንግስት’ በፈለጉት ስም ይጥሩት ግን ሁሉንም የሚያሳትፍ ስርዓት ያስፈልጋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ፕሮፌሰር መረራ “ትርጉም ያለው ልማት እና ብልጽግና መምጣት በሚቻልበት መንገድ የፖለቲካ ስርዓቱ ካልተዋቀረ በስተቀር፤ በግልጽ ቋንቋ የካድሬዎች አስተዳደር የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግር አይፈታም” ሲሉም ተደምጠዋል። ይህ የፖለቲካ ስርዓት “ለኢትዮጵያ ወጣቶች ተስፋ የሚሰጥ” መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል። 

“እኛ እስከገባን ድረስ ይሄ መንግስት  ‘ስልጣን መካፈል፣ የጋራ አስተዳደር እና አሳታፊ አስተዳደር እስከ ምርጫው ድረስ አታንሱብኝ’ የሚል ይመስለናል ያሉት የኦፌኮ ሊቀመንበር፤ “ሽግግሩን ከጠሉት በፈለጉት ስም ይጥሩት ግን ሁላችንንም የሚያቅፍ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያምንበት፣  የ’እኔ ነው’ የሚለው መንግስት በጣም ወሳኝ ነው። ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም” ሲሉ የፓርቲያቸውን እና የራሳቸውን አቋም በድጋሚ አስረግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)