በሃሚድ አወል
በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት መግባቱ የተነገረው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፤ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 1፤ 2015 ፍርድ ቤት ቀረበ። ጎበዜ ከሌሎች አምስት ግለሰቦች ጋር ፍርድ ቤት የቀረበው፤ በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ይህን የገለጸው የእነ ጎበዜን ጉዳይ ለመመልከት ዛሬ ተሰይሞ ለነበረው፤ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። ጋዜጠኛ ጎበዜን ጨምሮ ስድስት ተጠርጣሪዎች የቀረቡበት የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የተከፈተው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት በአቶ ሲሳይ አውግቸው ስም ነው።
ስድስቱን ተጠርጣሪዎች ችሎት ፊት ያቀረባቸው የፌደራል ፖሊስ፤ ግለሰቦቹ “የሽብር ድርጊት ተግባር በመፈጸም በንጹሃን ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው” በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጿል። ፖሊስ ስድስቱን ተጠርጣሪዎች “ህገ መንግስቱን እና ህግ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመቀየር በመንቀሳቀስም” ወንጅሏቸዋል።
ጋዜጠኛ ጎበዜን ወክለው ችሎት ፊት የቀረቡት ጠበቃ አዲሱ አልጋው፤ ፖሊስ “ማን በየትኛው የወንጀል ድርጊት የተሳተፈ እንደሆነ የገለጸው ነገር የለም” ሲሉ የተጠርጣሪዎች የወንጀል ተሳትፎ ፖሊስ በጽሁፍ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ አለመገለጹን ተናግረዋል። አቶ አዲሱ አክለውም ደንበኛቸው “ጥፋት ፈጽመዋል ከተባለ እንኳን በሚዲያ ስራቸው አማካኝነት ነው። ስለሆነም የምርመራ ሂደቱ መመራት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ነው” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ የቅድመ ክስ እስርን እንደሚከለክል ያስታወሱት ጠበቃ አዲሱ፤ የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ችሎቱን ጠይቀዋል። የፌደራል ፖሊስ በተጠርጣሪ ጠበቃ በኩል ለተነሳው ሃሳብ በሰጠው የመልስ መልስ “ጋዜጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ተጠርጥረው የተያዙት [ግን] ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር ተያይዞ አይደለም” ብሏል። የፌደራል ፖሊስን ወክለው ችሎት የተገኙት መርማሪ ፖሊስ አክለውም፤ “የጋዜጠኝነት ሙያን እንደሽፋን ተጠቅመው ሲሰሩ ነበር” የሚል ውንጀላን በጋዜጠኛ ጎበዜ ላይ አቅርበዋል።
የስድስቱም ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ አለልኝ ምህረቱ፤ “ተጠርጣሪዎቹ የትኛውን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት እንደተንቀሳቀሱ መርማሪ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ላይ አልገለጸም” ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል። መርማሪ ፖሊስ ለችሎት ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ፤ ተጠርጣሪዎቹን “ራሳቸውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ለማራመድ በማሰብ ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመቀየር” ወንጅሏቸዋል፡፡ ጠበቃ አለልኝ ግን “የፖለቲካ ድርጅት ሳይቋቋም የፖለቲካ ዓላማ በግለሰቦች በተናጥል የሚፈጸም አይደለም” የሚል መከራከሪያን አቅርበዋል።፡
በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አማካኝነት የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ “በጥብቅ” የተቃወሙት መርማሪ ፖሊስ፤ “የፖለቲካ ድርጅት ባይኖርም ‘ድርጊቱ ሽብር እስከሆነ ድረስ የሽብር ወንጀል ነው’ የሚል ጭብጥ ይዘን ነው [የቀረብነው]” ሲሉ የመልስ መልስ ሰጥተዋል፡፡ መርማሪው አክለውም ተፈጸመ የተባለው ወንጀል፤ “እጅግ ከባድ እና ውስብስብ” እንዲሁም “የሀገር አንድነት ላይ ችግር የሚፈጥር” በመሆኑ የዋስትናው ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አንድ ሰዓት ገደማ የፈጀውን የግራ ቀኝ ክርክር ካደመጠ በኋላ፤ በቀረበው የዋስትና እና የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ረቡዕ ግንቦት 2፤ 2015 ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዛሬው የችሎት ውሎ ስድስቱም ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸውን በአካል ተገኝተው ተከታትለዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]