በአማኑኤል ይልቃል
በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማት በአሁኑ ወቅት ያላቸውን ሀብት እና የሚሰጡትን የአገልግሎት አይነት የሚዳስስ ጥናት ሊካሄድ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት፣ የፌደራል የጤና ሚኒስቴር እና የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ በቅንጅት የሚያካሄዱት ይህ ጥናት፤ ተቋማቱ ያለባቸውን ችግር ለይቶ ትክክለኛውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ጥናት የሚደረግባቸው የትግራይ ክልል ጤና ተቋማት፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለማቆም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ “በተወሰነ መልኩ” አገልግሎት መስጠት የጀመሩ መሆናቸውን የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል። በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት “ታካሚዎች አገልግሎት እንዲያገኙ በሚል” ስራ ቢጀምሩም፤ ያላቸው ሀብት እና የጤና ባለሙያ ብዛትን በተመለከተ ግን የትግራይ ክልል ጤና ቢሮም ሆነ ሌሎች አጋር አካላት ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው የጥናቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ይብራህ አለማየሁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ወደ ትግራይ ክልል የሚመጡ የህክምና ቁሳቁሶች እና ሌሎች ድጋፎችን፤ በመረጃ ላይ ተመስርቶ በትክክል ለሚያስፈልጋቸው የጤና ተቋማት ማሰራጨት አለመቻሉን አስተባባሪው አስረድተዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ፤ ከዓለም የጤና ድርጅት በተገኘ የሶስት ሚሊዮን ብር ገደማ የገንዘብ ድጋፍ የጤና ተቋማቱን ወቅታዊ ሁኔታ የሚዳስስ ጥናት ለማድረግ መወሰኑንም አክለዋል።
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ በጦርነቱ ምክንያት በጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ጥናት ለማድረግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ የዓለም የጤና ድርጅት እቅዱን ባለመቀበሉ የአሁኑ ጥናት እንዲካሄድ መወሰኑን አቶ ይብራህ ገልጸዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ እቅድ ተቀባይነት ያላገኘው፤ በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለው የጤና ስርዓት በዓለም የጤና ድርጅት መለኪያ መሰረት “ደረጃ ሶስት” በሚባለው ምድብ ውስጥ በመውደቁ ምክንያት መሆኑን የጥናቱ አስተባባሪ ጠቁመዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት በወረርሽኝ፣ በአደጋዎች (disaster) እና በሰብአዊ ቀውስ ሳቢያ “የጤና አደጋ” (health Emergency) በተከሰተባቸው ሀገራት ያሉ የጤና አገልግሎት ሁኔታ በሶስት ምድቦች ይከፍላቸዋል። ድርጅቱ እነዚህን ምድቦች፤ በአንድ ሀገር ውስጥ ምላሽ የሚሰጥበትን ደረጃ ለመወሰን ይጠቀምባቸዋል። በ“ደረጃ ሶስት” ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ሀገራት፤ የዓለም አቀፉን የህብረተሰብ ጤና ተቋም “ከፍተኛ” ምላሽ የሚፈልጉ መሆናቸውን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በመንግስታቱ ድርጅት ስር የሚገኘው ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም ባለፈው ጥር ወር ላይ ባወጣው መረጃ፤ ስምንት ሀገራት በ“ደረጃ ሶስት” ምድብ ውስጥ መካተታቸውን አስታውቆ ነበር። በዚህ ምድብ ስር ከተካተቱት ሀገራት ውስጥ ዩክሬን፣ ሶርያ፣ አፍጋኒስታን እና የመን ይገኙበታል። የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙት ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያም በዚህ ምድብ ስር እንደሚገኙ የዓለም ጤና ድርጅት በወቅቱ ገልጿል። የ“ሰሜን ኢትዮጵያ” ክፍል በዚህ ምድብ ስር የተካተተው፤ በአካባቢው ባለው “ውስብስብ እና ተለዋዋጭ የሰብአዊ ሁኔታ” እንዲሁም በድርቅ ምክንያት እንደሆነ በመረጃው ላይ ተጠቅሷል።
ይህ አይነቱ ሁኔታ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው፤ በትግራይ ክልል ስለሚገኙ የጤና ተቋማት የአገልግሎት አቅርቦት ሁኔታ መረጃ ማሰባሰብ መሆኑ ከዓለም ጤና ድርጅት እንደተገለጸላቸው የጥናቱ አስተባባሪ አቶ ይብራህ ተናግረዋል። የፌደራል መንግስት እና የክልሉ ጤና ቢሮ በዚህ የድርጅቱ ሃሳብ መስማማታቸውን የጥናቱ አስተባባሪ አክለዋል። በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የቴክኒካል አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ሙኒር ካሳ፤ ጥናቱ የጤና ተቋማቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ ለመዳሰስ የሚካሄድ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ጥናቱ እስከ ቀጣዩ ሰኔ ወር መጀመሪያ ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀ ይህ ጥናት፤ በትግራይ ክልል ያሉ የጤና ተቋማትን አሁናዊ ሁኔታ በሚያሳዩ ስድስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ርእየ ኢሳያስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የጤና ተቋማቱ የአገልግሎት አቅርቦት፣ ሰራተኞች ያሉበት ሁኔታ እንዲሁም የመድኃኒት እና ህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት በጥናቱ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
የጥናቱ አስተባባሪ እና የትግራይ ክልሉ ጤና ቢሮ ባልደረባ የሆኑት አቶ ይብራህ፤ በጥናቱ የሚካተቱት የመጀመሪያ ደረጃ፣ አጠቃላይ እና ሪፈራል ሆስፒታሎች እንዲሁም የጤና ጣቢያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በጥናቱ ውስጥ 274 የጤና ተቋማት መካተት የነበረባቸው ቢሆንም፤ አሁን ለማጥናት ዝግጅት እየተደረገ ያለው ግን በ224ቱ ላይ ብቻ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል።
በጥናቱ ከማይካተቱ 50 የጤና ተቋማት መካከል የተወሰኑት የሚገኙት፤ በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ስር ያሉት የኢሮብ እና ዛላምበሳ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ የሚገኙ ማይጸብሪ፣ ታህታይ ጸለምቲ እና ላዕላይ ጸለምቲ አካባቢዎች መሆኑን የክልሉ ምክትል የጤና ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል። ከእነዚህ ቦታዎች በተጨማሪ በደቡባዊ ትግራይ የተወሰኑ የጤና ተቋማት እንዲሁም በምዕራብ ትግራይ የሚገኙት ሙሉ ለሙሉ በጥናቱ ውስጥ እንደማይካተቱ አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)