በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እና ሌሎች አምስት ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤት 14 የምርመራ ቀናት ፈቀደ  

በሃሚድ አወል

በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ትላንት ማክሰኞ ፍርድ ቤት በቀረበው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እና ሌሎች አምስት ግለሰቦች ላይ 14 የምርመራ ቀናት ለፖሊስ ተፈቀደ። የምርመራ ቀናቱን የፈቀደው ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 2፤ 2015 የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

ችሎቱ የምርመራ ቀናቱን የፈቀደው በተጠርጣሪዎች ጠበቆች በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ነው። ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን ውድቅ ያደረገው፤ መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ባስገባው የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻ “ተጠርጣሪዎቹ በመሩት እና ባስመሩት የሽብር ድርጊት በርካታ ንጹሃን ዜጎች እንዲሞቱ፣ በርካታ የህዝብ እና የመንግስት ንብረቶች እንዲወድሙ [ሆኗል]” የሚል መከራከሪያ በማቅረቡ ነው። 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዛሬው ውሎው፤ ተፈጸመ በተባለው ወንጀል የሰው ህይወት ካለፈ የሚጣለው የቅጣት መጠን ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል። የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከሶስት ዓመት በፊት የወጣው አዋጅ የተፈጸመው ተግባር “ሰውን መግደል” የሚጨምር ከሆነ፤ “ከአስራ አምስት ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይሞ በሞት” እንደሚያስቀጣ ያትታል። 

በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርዓት መሰረት፤ አንድ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት 15 ዓመት እና ከዚያ በላይ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ከሆነና በወንጀል ድርጊቱ የሰው ህይወት የጠፋ ከሆነ ዋስትና እንደማይፈቀድ ያብራራል። የስነስርዓት ህጉን የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፤ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኋላ ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል። ጋዜጠኛ ጎበዜን ጨምሮ ስድስቱም ተጠርጣሪዎች በተገኙበት በጽህፈት ቤት በኩል የተካሄደው የዛሬው የችሎት ውሎ የተጠናቀቀው፤ ለግንቦት 16፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)