በአዲስ አበባ አንድ ሺህ ገደማ የግል ትምህርት ቤቶች፤ ከ20 እስከ 100 በመቶ የሚደርስ የክፍያ ጭማሪ ለማድረግ “ፕሮፖዛል” ማቅረባቸው ተነገረ  

በአማኑኤል ይልቃል

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አንድ ሺህ ገደማ የግል ትምህርት ቤቶች፤ በተማሪዎች ወርሃዊ ክፍያ ላይ ከ20 እስከ 100 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ለማድረግ “ፕሮፖዛል” ማቅረባቸውን የከተማዋ የትምህርት እና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። ትምህርት ቤቶቹ “ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደርሱ” ጭማሪውን መተግበር እንደማይችሉም አስጠንቅቋል።

ባለስልጣኑ ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የግል እና መንግስታዊ ላልሆኑ ትምህርት ቤቶች ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 2፤ 2015  በጻፈው ደብዳቤ ነው። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት እውቅና የመስጠት እና አሰራራቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ነው። 

መስሪያ ቤቱን ባቋቋመው አዋጅ መሰረት፤ ባለስልጣኑ በአዲስ አበባ ውስጥ ለሚሰጠው የትምህርት አገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያ “የወላጆችን የመክፈል አቅም ያገነዘበ እንዲሆን” የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ፤ መስሪያ ቤቱ ከትምህርት ከተቋማት ጋር እንደሚመካከር በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። 

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ዘበናይ ኃይለጊዮርጊስ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ለመስሪያ ቤቱ የማስታወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚህም መሰረት በከተማዋ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች በመጋቢት ወር ለመስሪያ ቤቱ የዋጋ ጭማሪ “ፕሮፖዛል” ማቅረባቸውን ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት 1,558 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ በቀጣዩ 2016 የትምህርት ዘመን ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችላቸውን “ፕሮፖዛል” ያቀረቡት 1,257 መሆናቸውን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፍቅርተ አበራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። እነዚህ ተቋማት በዚሁ “ፕሮፖዛላቸው” ላይ በምን ያህል መጠን ጭማሪ ለማድረግ እንዳቀዱ እና ይህንን የሚያደርጉበትን ምክንያት በዝርዝር ማስፈራቸውን ጠቅሰዋል። 

በተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ አሰራር መሰረት፤ የትምህርት ተቋማት በሶስት ምክንያቶች የክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል። “አላቂ የማስተማሪያ ግብአቶችን ለማሟላት፣ የመምህራን ደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ እና የትምህርት ተቋሙን የጥራት ደረጃ ለማሳደግ” የሚሉ ምክንያቶች ተቀባይነት ያላቸው ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የትምህርት ተቋማቱ ሊያደርጉ ያሰቡትን ጭማሪ በተመለከተ፤ ከተማሪ ወላጆች ውስጥ 51 በመቶ ያህል የሚሆኑት በተገኙበት ውይይት የማድረግ እና ተስማምቶ የመወሰን ግዴታ እንዳለባቸው ወ/ሮ ፍቅርተ ጠቁመዋል። የትምህርት ተቋማቱ በሚጠሩት የመጀመሪያ ውይይት ላይ የሚገኙ ወላጆች ብዛት ከ51 በመቶ በታች ከሆነ ስብሰባው መበተን እንዳለበት በባለስልጣኑ አሰራር ላይ ተቀምጧል። ተቋማቱ ለሁለተኛ ጊዜ በሚጠሩት ስብሰባ ላይ ግን ሊደረግ የታሰበው ጭማሪ በስፍራው በተገኙት ወላጆች መጽደቅ እንደሚችል አሰራሩ ይደነግጋል። 

እስካሁን ድረስ 1,031 ትምህርት ቤቶች በሚያደርጉት የክፍያ ጭማሪ ላይ ከወላጆች ጋር ተስማምተው ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማቅረባቸውን የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 394ቱ፤ ከ21 እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ለማድረግ ከወላጆች ጋር የተስማሙ መሆናቸውንም አስረድተዋል። በተማሪዎች ክፍያ ላይ ከ41 እስከ 60 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ለማድረግ ማቀዳቸውን ያስታወቁ ትምህርት ቤቶች ብዛት ደግሞ 394 መሆኑን አክለዋል። 

ከ81 በመቶ በላይ ጭማሪ ለማድረግ ከተማሪ ወላጆች ጋር መስማማታቸውን ለባለስልጣኑ የገለጹ ትምህርት ቤቶች 34 መሆናቸውን ወ/ሮ ፍቅርተ ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ከ100 በመቶ በላይ ጭማሪ ለማድረግ ያቀዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። እቅዳቸውን አቅርበው ውይይት ካደረጉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 226ቱ፤ በሚያደርጉት የጭማሪ መጠን ላይ ከወላጆች ጋር እስካሁን መስማማት አለመቻላቸውን ምክትል ስራ አስኪያጇ አስረድተዋል።

ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል ብዙ ቅርንጫፍ እና የተማሪ ቁጥር ያላቸው እንደሚገኙበት የሚናገሩት ወ/ሮ ፍቅርተ፤ “እስከ እሁድ ድረስ መልሳችሁ ቁጭ ብላችሁ ተመልከቱት ብለናል” ሲሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ገልጸዋል። የእርሳቸው ፊርማ በያዘው እና ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 2፤ 2015 ለግል እና መንግስታዊ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች በተሰራጨው ደብዳቤ ላይም ይኸው ትዕዛዝ ተካትቷል። 

በተማሪዎች ክፍያ ላይ የሚደረገው ጭማሪ “በትምህርት ቤቶች እና በወላጆች ውይይት እና መግባባት መሰረት” የሚደረግ እንደሆነ የጠቆመው ደብዳቤው፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው ምልከታ ግን በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች “ከወላጆች ጋር በቂ ስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ” አረጋግጬያለሁ ብሏል። ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪን በተመለከተ “ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደረስ ወደ ተግባር መግባት” እንደማይችሉ ያስታወቀው መስሪያ ቤቱ፤ ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ “አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ” እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። 

የትምህርት እና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጇ ወ/ሮ ፍቅርተ፤ እስከ መጪው እሁድ ግንቦት 6፤ 2015 ድረስ ባሉት ቀናት ውይይት አድርገው ስምምነት ላይ በማይደርሱ ትምህርት ቤቶች ላይ ባለስልጣኑ “በጉዳዩ ላይ እንደሚገባ” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “በእርግጠኝነት እኛ ስንገባ፣ ስናወያያቸው ይስማማሉ” ሲሉ ትምህርት ቤቶች የሚያደርጉት ጭማሪን በተመለከተ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ እምነታቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)