በሃሚድ አወል
የመንግስት የልማት ድርጅቶች በራሳቸው የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ሲፈጽሟቸው የነበሩ ግዥዎች፤ በፌደራል መንግስት የግዥ እና ንብረት አስተዳደር ስርዓት ስር እንዲሆን የሚያደርግ የአዋጅ ረቂቅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ። የአዋጁ ረቂቅ በመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል የሚፈጸመውን የቀጥታ ግዥም ያስቀራል።
በግዥ እና በንብረት አስተዳደር ላይ ማሻሻያዎችን ያደረገው የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ የቀረበው፤ ዛሬ ግንቦት 3፤ 2015 ዓ.ም በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ላይ ነው። የአዋጅ ረቂቁን ማብራሪያ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በንባብ ያሰሙት የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፤ “በአፈጻጸም ወቅት ካጋጠሙ ችግሮች በመነሳት” ነባሩን የፌደራል የመንግስት ግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ማሻሻል እንዳስፈለገ ተናግረዋል።
አቶ ተስፋዬ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ በ2001 ዓ.ም የወጣውን ነባሩን አዋጅ የሚያሻሽለው አዲሱ ህግ ያስተዋወቃቸውን አዳዲስ ነገሮች ለፓርላማ አባላቱ ጠቁመዋል። የመንግስት ተጠሪውን የጠቀሱት የመጀመሪያው ጉዳይ፤ የአዋጁ ተፈጻሚነት ወሰን የመንግስት የልማት ድርጅቶችን እንዲያካትት መደረጉን ነው። አዲሱ አዋጅ “የተወዳዳሪነት ሚናቸው ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር”፤ የልማት ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከ30 ዓመት በፊት በወጣው የመንግስት የልማት ድርጅቶች አዋጅ መሰረት የተቋቋሙ ናቸው። በአዋጁ መሰረት የመንግስት የልማት ድርጅት የሚባሉት፤ በመንግስት ሙሉ ባለቤትነት፤ የማምረት፣ የማከፋፈል አገልግሎት የመስጠት ወይም ሌሎች የኢኮኖሚ ተግባሮችንና ከእነዚሁ ጋር የተያያዙ ስራዎችን በንግድ መልክ ለማካሄድ የተቋቋሙ ናቸው። ድርጅቶቹ በራሳቸው ገቢ አመንጭነት የሚተዳደሩ መሆናቸው፤ ከመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተለዩ ያደርጋቸዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች የግዢ እና የንብረት አስተዳደር ስርዓት የሚመራው፤ ራሳቸው ድርጅቶቹ በሚዘረጉት አሰራር ነው። ድርጅቶቹ በተለያየ የግዥ አፈጻጸም የህግ ማዕቀፎች መመራታቸው፤ “በፌደራል ደረጃ የመንግስት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ወጥነት እንዳይኖረው” ማድረጋቸውን በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል። “በመንግስት ገንዘብ የሚፈጸሙ ግዥዎችን ወጥ እንዲሆኑ ማድረግ፤ የተለያየ የግዥ ስርዓትን ከመከተል ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ለቁጥጥር የማይመች አሰራር ለማስቀረት ያስችላል” ሲል የአዋጅ ማብራሪያው አክሏል።
ይህን አዲስ አሰራር በተመለከተ በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ የተገኙ፤ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። አቶ ባያብል ሙላቴ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የግዥ እና ንብረት አስተዳደር ስርዓት መቀየር “ለምን አስፈለገ?” ሲሉ ጠይቀዋል። “ወጥ እንዲሆን በሚል በመንግስት የግዥ ስርዓት ውስጥ መታቀፍ አለባቸው የሚለው፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አሰራር የሚቆልፍ፤ እንዳይወዳደሩ የሚያደርግ ይመስለኛል። በደንብ የተጠና አይመስለኝም” ሲሉም አቶ ባያብል ተናግረዋል።
በፓርላማው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ባያብል፤ “የመንግስት የግዥ ስርዓት የሚያገለግለው በበጀት ለሚተዳደሩ መስሪያ ቤቶች ነው” ሲሉ በንግግራቸው አስታውሰዋል። የአዋጅ ረቂቁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በደንብ እንደሚለከተውም አሳስበዋል።
አቶ ተስፋሁን ቦጋለ የተባሉ ሌላ የፓርላማ አባል፤ በአዲሱ አዋጅ የዋጋ ማቅረቢያ (pro forma) የግዥ ዘዴ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ በማንሳት አስተያየት ሰጥተዋል። በአዋጁ ረቂቁ ላይ በዋጋ ማቅረቢያ (pro forma) የሚፈጸም ግዥ፤ በዓመታዊ ዕቅድ ውስጥ መካተት እንደሚኖርበት ሰፍሯል። በዕቅድ ያልተያዙ ግዥዎችን በዋጋ ማቅረቢያ መግዛት የሚቻለው፤ በመስሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ሲፈቀድ ብቻ መሆኑም በረቂቁ ተቀምጧል።
አቶ ተስፋሁን ይህን የአዋጁን ድንጋጌ “መቶ ፐርሰንት አልቀበለውም” ሲሉ ተቃውመውታል። የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን የመንግስት የልማት ድርጅቶችንም እንዲያካትት መደረጉን ያስታወሱት አቶ ተስፋሁን፤ “በነበረው ልምድ ብዙ የልማት ድርጅቶች የከሰሩት ኃላፊዎች በሚያደርጉት ግዥ ሂደት ነው” ሲሉ የተቃወሙበትን ምክንያት አስረድተዋል።
አዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ ያደረገበት ሌላኛው ጉዳይ፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚፈጸሟቸውን የቀጥታ ግዥዎችን የተመለከተ ነው። የመንግስት መስሪያ ቤቶች “ዕቃዎችን፣ የግንባታ ዘርፍ ስራዎችን፣ የምክር እና ሌሎች አገልግሎቶችን” ወጪ በመሸፈን ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለማግኘት በሚደርጉት ውል ላይ፤ አሁን በስራ ላይ ያለው የግዥ ህግ ተፈጻሚ አይሆንም ነበር።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ይህን የአዋጅ ድንጋጌ ሽፋን በማድረግ፤ “ከህጉ ዓላማ ውጪ፣ እርስ በእርሳቸው የንግድ ልውውጥ በስፋት ሲያካሂዱ ይስተዋላል” ሲል የአዲሱ አዋጅ ማብራሪያ ያስገነዝባል። “ይህ የነጻ ገበያ መርህ የሆነውን የንግድ ውድድርን የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ፤ የመንግስት ገንዘብን ለብልሹ አሰራር እንዲጋለጥ ምክንያት በመሆኑ ቀሪ እንዲሆን ተደርጓል” ሲል ከማሻሻያው ጀርባ ያለውን አመክንዮ አስረድቷል።
አዲሱ አዋጅ በመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል የሚፈጸመውን የቀጥታ ግዥ የሚያስቀር ድንጋጌ ማካተቱ፤ ከአንድ የፓርላማ አባል ጥያቄ ቀርቦበታል። አቶ ባርጠማ ፈቃዱ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ “መስሪያ ቤቱ ወይም አቅራቢው ድርጅት ብቸኛ አቅራቢ (sole agent) ከሆነ ምን ሊደረግ ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። አቶ ባርጠማ ጥያቄቸውን የአዋጅ ረቂቁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ እንዲመለከተው አሳስበዋል። ይህን መሰል ጥያቄዎች ያስተናገደው “የፌደራል የመንግስት ግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ” ማሻሻያ፤ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)